ዜና፡ መንግስት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን በአስቸኳይ እንዲለቅና በአሀገር ውስጥና በውጭና የሚገኙ የፕሬስ አባላትን ማዋከብ እንዲያቆም ሲፒጄ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት፣ 5/ 2015 ዓ.ም፡- መንግስት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን በአስቸኳይ እንዲለቅ እና በአሀገር ውስጥና በውጭና የሚገኙ የፕሬስ አባላትን ማዋከብ እንዲያቆም የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ ጠየቀ፡፡

ተቋሙ ትላነንት ባወጣው መግለጫ የአማራ ድምፅ ዩቱዩብ ቻናል መስራች የሆነው ጎበዜ ሲሳይ ሚያዝያ 28፤ 2015 ከጂቡቲ በመንግስት ቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውሶ ጠበቃው አዲስ አልማው ጎበዜ ከጅቡቲ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ መሰጠቱን እና በአዲስ አበባ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ በእስር ላይ እንደሚገኝ ለሲፒጄ መናገሩን ገልጧል።

የጎበዜን እስር በተነገረበት የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ፣ ጎበዜ በጁቡቱ በቁጥጥር ስር የዋለው በጅቡቲ ባለስልጣናት እና በዓለም አቀፉ ፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ትብብር እንደሆነ መግለፁ ይታወሳል። በዚህ ጉዳይ ላይ በኢ-ሜይል ለሲፒጄ ምላሽ የሰጡ የኢንተርፖል ተወካይ፤ ስለ ጎበዜ ዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት “በዳታቤዙ” ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለው እና “ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋልም ሆነ አሳልፎ የመስጠት ስልጣን እንደሌለው” ገልፀውልኛል ሲል ሲፒጄ በመግለጫው አክሎ ገልጧል፡፡

ፖሊስ በሽብርተኝነት እና ስሙ ያልተገለጸ ታጣቂ ቡድን ፕሮፖጋንዳ በመምራት እንደጠረጠረው የጠቀሰው ሲፒጄ ጎበዜ ወደ ጂቡቲ የተሰደደው የጸጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ሚያዝያ 22 ቀን 2015 ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ መሆኑን ጠበቃው መግለፁን በመግለጫው አካቷል፡፡

ከሰሃራ በረሃ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት የሲፒጄ ተወካይ ሙቶኪ ሙሞ፣ “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን ዝም ለማሰኘት ሲል በድፍረት ድንበር አቋርጧል፤ እስሩ ደህንነት ፈልገው ከሀገራቸው በተሰደዱ ጋዜጠኞች ላይ ፍራቻ ይፈጥራል፤  ጎበዜ በአስቸኳይ ሊፈታ ይገባል፣ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ባለስልጣናትም በቁጥጥር ስር ስለዋለበት እና ተላልፎ ስለተሰጠበት ሁኔታ ማብራሪያ መስጠት አለባቸው” ብለዋል።

ሲፒጄ ስለ ጎበዜ እስር ለፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ ጥያቄ አቅርቦ፤ ምላሽ አለመስጠታቸውን ገልፆ ነገር ግን በጽሁፍ መልእክት በአማራ ክልል ከአንድ ባለስልጣን ሞት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር መዋሉን እና በሽብርተኝነት መጠርጠሩን ግን በጋዜጠኝነት ስራው ዒላማ አለመደረጉን ገልፀዋል ብሏል።

በተጨማሪም ከጅቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሳኢድ ኑህ ሐሰን እና ከሀገሪቱ የህዝብ ደህንነት ምክትል ዳይሬክተር ኦማር ሀሰን እንዲሁም ከማስታወቂያ ሚኒስትር ሬድዋን አብዱላሂ ምላሽ ማግነት አለመቻሉን አስታውቋል፡፡

ጎበዜ በቁጥጥር ስር ከመዋሉ በፊት የሰራቸው ዘገባዎች፤ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት “ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ” መወሰኑን ተከትሎ በክልሉ የነበሩ አለመረጋጋቶች ላይ ያተኮሩ እንደነበሩም ሲፒጄ አስታውሷል።

የጋራ ግብረ ሃይሉ ጎበዜን ጨምሮ 47 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስራ ማዋሉን ያስታወሰው መግለጫው አምስት ጋዜጠኞች ማለትም መስከረም አበራ፣ ዳዊት በጋሻው፣ ቴዎድሮስ አስፋው፣ ገነት አስማማውና አሰፋ አዳነ በእስር ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.