አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22/ 2015 ዓ.ም፡- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፌደራል መንግስት የትግራይ ክልል ባለስልጣናት “የሀገሪቱን ህግ እንዲያከብሩ፣ ህገ መንግስቱን እንዲያከብሩና እንደ አንድ የኢትዮጵያ ክልል እንዲሆኑ” ለማሳመን እየሞከረ ነው አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የቻይና መንግስት ሚዲያ ከሆነው ከሲጂቲኤን( CGTN) ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ሰላም “የብልጽግና መሰረት ነው”፤ መንግስትም “ሰላም ለማምጣት እየሰራ ነው” ብለዋል።
“ሰላም የብልጽግና መሰረት ነው፣ ሰላም የምግብ አቅርቦትን በማረጋገጥ በቂ ምግብ ለማምረት ለምትፈልግ ሀገር መሰረት ነው። ሰላም ከሌለ ራዕያችንን እውን ማድረግ የምንችልበት ምንም አይነት መንገድ ስለሌለ ለሰላም እየሰራን ነው” ሲሉ ጠ/ሚ አብይ ተናግረዋል። አክለውም የትግራይ ባለስልጣናት የመንግስትን ፍላጎት ተረድተው “በህገ መንግስታቸው አምነው ቢሰሩ ሰላም የሚሰፍን ይመስለኛል” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስም ሳይጠቅሱ “ከግራ እና ከቀኝ አያሌ ጣልቃ ገብነት” እንዳለ ገልፀው “አንዳንድ ጊዜ በጣም ከባድ ነው” ሲሉም ተናግረዋል ።
“ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን መፍታት እንደምንችል መረዳት አለባቸው፣ ሩቅ ያሉትን ከመስማት የራሳችንን ህግ፣ ባህል ማክበር የተሻለ ነው። ያን ማድረግ ከቻልን ሰላም እንደሚሰፍን ተስፋ አደርጋለሁ።” ብለዋል፡፡
ጠ/ሚር አብይ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ሃይል ቁጥጥር ስር ባሉ እንደ ሽሬ፣ አክሱም እና አድዋ ከተመዎች መንግሥት ሰብዓዊ እርዳታ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠ/ሚ ይህን ያሉት በአፍሪካ ህብረት መሪነት በኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች እና በትግራይ ባለስልጣናት መካከል እየተደረገ ያለው የሰላም ድርድር “እስከዚህ ሳምንት ድረስ” በተራዘመ ወቅት ነው።
የሰላም ንግግሮሩ ማክሰኞ ጥቅምት 15 ቀን ተጀምሮ እሁድ ጥቅምት 20 ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር። ስለ ሰላም ድርድሩ ቀን መራዘም እና እስካሁን ስላለው ሂደቶች ከአፍሪካ ህብረት የተሰጠ ይፋዊ መግለጫም የለም።
የአምሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ የንግግሮቹ መራዘም በተደራዳሪዎቱ መካከል ያለውን “ርቀት” ያሳያል ብለዋል።
“ይህ የሚያመለክትው ፓርቲዎቹ ደቡብ አፍሪካ ሲደርሱ በመካከላቸው ልዩነትነ ቢኖርም፣ አብረው ለመቀመጥ ፍቃደኞች በመሆናቸው ፓርቲዎቹ በልዩነታቸው ላይ ተወያይተው በመካከላቸው ያለውን ርቀት አጥብበው መቀጠላቸው ተስፋ ያደረግንበት ነው” ብለዋል፡፡
ሆኖም አሜሪካ “ሁለቱ አካላት መነጋገራቸውን መቀጠላቸው ጥሩ ነገር ነው” ብላ እንደምታምን ተናግራለች፡፡
“የድርድሩ አላማ በጣም ቀላል ነው፤ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ለተቸገሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሰብዓወዊ እርዳታ እንዲደርስ፣ ተጨማሪ እርምጃዎች፤ ማለትም ሰላማዊ ዜጎችን ለመጠበቅ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ እና የኤርትራን ከሰሜን ኢትዮጵያ መውጣት ማየት” ሲልም አክሏል፡፡
በአፍሪካ ህብረት የሚመራው የሰላም ድርድር ማክሰኞ ጥቅምት 15፣ 2015 ዓ.ም ተጀምሮ እሁድ ጥቅምት 20፣ 2015 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ቃል አቀባይ ቪንሴንት ማግዌንያ ተናግረውም ነበር፡፡
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበሩ “በትግራይ ክልል አስቸኳይ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እና የሰብአዊ አገልግሎት እንደገና እንዲጀመር” ጥቅምት 5 ቀን ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ የሰላም ድርድሩ ከፍተኛ መነቃቃትን አግኝቷል። አንቶኒ ብሊንከንም የሊቀመንበሩን መግለጫ በመደገፍ በዚህ ሳምንት ባወጡት መግለጫ “በአፋጣኝ ተኩስ ማቆም ቅድሚያ ሊሰጠዉ የሚገባ ነገር ነዉ” ያሉ ሲሆን በተጨማሪም “ልዑካን ቡድኑ ለተቸገሩት ሁሉ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ፣ ሰላማዊ ዜጎችን ለመጠበቅ በሚወሰዱ እርምጃዎች እና ኤርትራ ከሰሜን ኢትዮጵያ በምትወጣበት ጊዜ ላይ እንዲስማሙ” ጠይቀዋል።
ውይይቱ የአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ እና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አንዲሁም የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፉምዚሌ ምላምቦ ንጉካ መሪነት እየተካሄደ ነው።
የአፍሪካ ህብረት መረጃ አንደሚያመላክተው የኢጋድ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአሜሪካ ተወካዮች በውይይቱ ላይ በታዛቢነት እየተሳተፉ ነው፡፡አስ