አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29/ 2015 ዓ.ም፡- መንግሥት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት ሲባል የየክልሉን ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያስችላቸውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ መጀመሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡
አገልግሎቱ ትላንት ባወጣው መግለጫ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አባላት እንደ ምርጫቸውና እንደ ፍላጎታቸው በመከላከያ፣ በፌደራል ፖሊስ ወይም በክልል ፖሊስ አባልነት መካተት ይችላሉ ሲል አስታውቋል፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይም ከልዩ ኃይል አመራሮችና አባላት ጋር ከመግባባት ላይ ተደርሷል ብሏል።
“ቀደም ብሎም በሁሉም ክልል አመራሮች ጥናት ተደርጎበት፣ በተገኘው ውጤትም ያለምንም ልዩነት ውሳኔው ስምምነት ተደርሶበታል። ይህ ተግባር እንዲፈፀም መላ ህዝባችንም ሲጠይቅ ቆይቷል። ይሄንን ተከትሎም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል” ሲል መግለጫው ገልጧል።
የሂደቱ ዋና ዓላማ የትኛውንም ልዩ ኃይል ትጥቅ ማስፈታት አይደለም ያለው መግለጫው “ልዩ ኃይሉ ትጥቁን ይዞ እና የተሻለ ዐቅም ተፈጥሮለት በምርጫው መሠረት የክልል ፖሊስን፣ የፌደራል ፖሊስን ወይም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀል ማድረግ ነው” ብሏል። በዚህ ሂደት መካተት የማይፈልግ ማንኛውም የልዩ ኃይል አባል ካለ መብቱ ተጠብቆ ወደ መደበኛ የሲቪል ሕይወት እንዲገባ መንግሥት አስፈላጊውን የማቋቋም ሥራዎችን እንደሚሰራ፣ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
“የክልል ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማስገባት ፕሮግራም በመላ ሀገሪቱ የሚተገበር ነው። ሥራውም በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኝ ነው” ያለው አገልግሎቱ ሆኖም በአማራ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ የልዩ ኃይል ክፍሎች ውስጥ፤ በአንድ በኩል የመልሶ ማደራጀት ሥራውንና ዓላማውን በአግባቡ ባለመረዳት፤ በሌላ በኩል የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ሆን ብለው በሚነዙት የሐሰት ወሬ በመጠለፍ ሂደቱን የሚያውኩ ተግባራት ታይተዋል ሲል ገልጧል፡፡
ከመግለጫው የመልሶ ማደራጀቱ መርሐ ግብር በአማራ ክልል ብቻ እየተካሄደ ነው፤ ሕወሐት ትጥቅ ሳይፈታ እንዴት የክልሉ ልዩ ኃይል ትጥቅ ይፈታል የሚሉትና የሀሰት መረጃዎች እየተነዙ ነው ሲል ጠቅሶ እነዚህ አጀንዳዎች ሂደቱን ለማደናቀፍ በሚፈልጉ ኃይሎች ነው እየተናፈሰ የሚገኘው ሲል ገልጧል፡፡
ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማስገባት ተግባር በሚፈጸምበት ጊዜ፣ በክልሎች አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሁሉም ቦታዎች ሥምሪት ወስዷል ሲል የገለፀው መንግስት ሕወሐት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ እየተደረገ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብሏል።
የክልል ልዩ ኃይልን በተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች የማካተት ውሳኔና የተግባር እንቅስቃሴ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የሚከናወን ነው። ይህ አካሄድ የኢኮኖሚ ዐቅማችንን በማሰባሰብ የሠራዊታችንን የሥልጠና፣ የትጥቅ እና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ አለው። ይሄንን በመረዳትም በሁሉም ክልሎች ሂደቱ በመግባባትና በውይይት እየተከናወነ ይገኛል ብሏል።
ይህን የመንግስት ውሳኔ ተከትሎ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቋማቸውን እየገለፁ ይገኛል፡፡ ኢዜማ ይህ ውሳኔ በእርግጥም ከመዘግየቱ በስተቀር ተገቢነቱ ላይ ጥያቄ ሊነሳበት አይገባም ሲል በውሳኔው መስማማቱን አስታውቋል ፡፡ አብን እና ባልደራስ በበኩላቸው በመቃወም የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡
ኢዜማ የክልል ልዩ ኃይሎችን ወደ ፌደራልና የክልል ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ውስጥ የማስገባት በጎ ጅምር አላስፈላጊ ውዥንብር ፈጥሮ ሌላ ሀገራዊ አደጋ እንዳይጋብዝ ጥንቃቄ ይፈልጋል ሲል ሃሳቡን አጋርቷል፡፡ ፓርቲው አክሎም የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ህጋዊ የፀጥታ መዋቅር ሥር መግባታቸውን ከልባችን የምንደግፈው ውሳኔ ሆኖ እያለ ፤ አተገባበሩ ፈንጅ የማምከን ያህል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ፣ በተለይም በሀገራችን ሥር ከሰደደው የዘውግ ፖለቲካ ጡዘት አኳያ አፈጻጻሙ በተጠና መልኩ መኾን አለበት ሲል አሳስቧል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)በበኩሉ መንግስት ያሳለፈውን ውሳኔ በፅኑ ተቋውሞታል፡፡ አብን ትላንት ባወጣው መግለጫ ከዚህ ቀደም አቋሙን በገለፀበት መግለጫ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በድንገት እና ያለበቂ የጸጥታ ዋስትና ማፍረስ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የአማራ ክልል አካባቢዎችን ተገማች እና ቀጥተኛ ለሆነ ጥቃት ተጋላጭ የሚያደርግ ነው ሲል ስጋቱን መግለፁን አስታውሶ የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ውሳኔውን በአፋጣኝ እንዲቀለብስ እና ከአማራ ክልል መንግስት እና ከክልሉ ሕዝብ ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት እና ምክክር እንዲደረግ እና የክልሉን እና የሃገራችንን ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ መልኩ ውሳኔው እንዲከለስ አሳስቧል፡፡
ኃይሉ ያለ በቂ ዝግጅት ፣ ውይይት፣ የጋራ መግባባትና መተማመን ሳይደረስ በድንገት እና ያለበቂ የጸጥታ ዋስትና ለማፍረስ መንግስት ያሳለፈው ውሳኔ እና ውሳኔውን ለማስፈጸም እየሄደበት ያለው መንገድ ኃላፊነት የጎደለው እና ዳፋው በአማራ ክልል ብቻ ሳይወሰን በሃገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አለመረጋጋት የሚፈጥር ነው ያለው አብን፣ ክልሉን እና ሃገራችን ኢትዮጵያን ወደ ሌላ የቀውስ አዙሪት የሚከት አደገኛ አካሄድ መሆኑን ፓርቲያቲው ጠቁሟል፡፡
ሌላ የመንግስትን ውሳኔ በመቀዋወም መግለጫ ያወጣው ፓርቲ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ነው፡፡ ፓርቲው በመግለጫው በመርህ ደረጃ የክልል ልዩ ኃይል መፍረስ እንዳለበት እና ሀገራዊ በሆነ ተክለ ሰውነት በተላበሰ የመከላከያ ሠራዊት መጠናከር እንዳለበት እንደሚያምን ጠቅሶ ነገር ግን ከወቅታዊ ሁኔታዎች አንፃር እና አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ጉዳዩ ተቀባይነት የለውም ሲል አቋሙን አንፀባርቋል፡፡
ባልደራስ በአቋም መግለጫው የአማራ ክልል መንግሥት ይህን የአማራ ህዝብን ለአደጋ አጋላጭ የሚያደርግ ትጥቅ የማስፈታት ውሳኔ እንዲቃወምና ተግባራዊ እንዳያደረግ በማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ባልደራስ በጥብቅ አሳስቧል፡፡ አስ