አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በህወሓት ህጋዊ ሰውነት ዙሪያ ያስተላለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) እና የትግራይ አካታች ጊዚያዊ አስተዳደር በተናጠል ውሳኔውን እንደማይቀበሉት የሚያመላክት መግለጫ አውጥተዋል።
ህወሓት ባወጣው መግለጫ በቦርዱ የተሰጠው ውሳኔ ቅቡልነት የሌለው፣ በፕሪቶርያ የተደረሰው ስምምነትና ህግን መሰረት ያላደረገ ነው ሲል ተችቷል። የፕሪቶርያውን ስምምነት የህዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር-ቤት፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ኣቃቢ ሕግ፣ የክልል መንግስታት እና የከተማ አስተዳደሮች ለስምምነቱ እውቅናና ድጋፍ መስጠታቸውን መግለጫው አውስቷል።
ነገር ግን የምርጫ ቦርድ ስምምነቱን የሚደግፍ ተግባር ሳይሆን የሚያደናቅፍ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ሲል ኮንኗል። በቦርዱ የተላለለፈው ውሳኔ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት የማይቀበል፣ እየተጠናከረ በመሄድ ላይ ያለውን የሰላም ስምምነቱ ትግበራ ባለቤት አልባ የሚያደርግ፣ ከጦርነቱ ወደ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ለሚገቡ ሃይሎች መደገፍ እና ማበረታታት ሲገባ ድርጅቶችን በማፍረስ ቀጣይ ሰላም እንዳይረጋገጥ የሚያደርግ ነው ብሎ እንደሚያምን አስታውቋል።
በአጠቃላይ ህወሓት የቦርዱን ውሳኔ እንደማይቀበለው እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚወያይበት አስታውቆ የምርጫ ቦርድ ውሳኔውን እንደገና በማጤን የፕሪቶርያ ስምምነትና ሌሎች የፌደራል ተቋማት ያስተላለፉትን ውሳኔዎች መነሻ በማድረግ እንዲያስተካክል ጠይቋል፡፡
የፌደራል መንግስትም ብሄራዊ የምርጫ ሊያሳድረው የሚችለውን አላስፈላጊ ጫና በመመዘን የፕሪቶርያው ስምምነት በሁሉም የመንግስት ተቋማት እና አካላት እንዲከበር ሀላፊቱን ይወጣ ብሏል። የቦርዱ ውሳኔ እንደገና ታይቶ ከህ.ወ.ሓ.ት ህጋዊ ሰውነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች ያሉትን ህጋዊና ፖለቲካዊ አማራጮች ተጠቅሞ በቅድመ-ጦርነት ወደ ነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ ሊያደርግ ይገባል ብሏል።
በተጨማሪም የፕሪቶርያ ስምምነት እንዲሳካ ከፍተኛ ኣስተዋፅኦ ያደረጉ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በአጠቃላይ የአፍሪካ ህብረት ደግሞ በተለይ ሂደቱ የሚያደናቅፍ እና አደጋ ውስጥ የሚከት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ በፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት ተቃኝቶ እንዲስተካከል የድርሻችሁን እንድትወጡ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
በተመሳሳይ የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የሰላም ተስፋ ከመደገፍ ይልቅ የሰላም ስምምነቱ ዋናው ባለቤት የሆነውን ህወሓት ህልውና እንዳይኖረው ለማድረግ ያስተላለፈውን ውሳኔ በሕግም በፖልቲካም ተቀባይነት የለውም ሲል ተችቷል።
የግዜያዊ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ የቦርዱ ውሳኔ የሰላም ስምምነቱ ባለቤት አልባ የሚያደርግ፣ ህወሓትን ወክለው በትግራይ አካታች ጊዚያዊ አስተዳደር እየተሳተፉ ያሉት ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች እውቅናን በመንፈግ የጊዚያዊ አስተዳደሩ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል እንዲሁም አጠቃላይ የሰላም ስምምነቱን የሚፈታተን ነው ሲል በምክንያትነት ዘርዝሯል።
ምርጫ ቦርድ ቴክኒካዊ በሆነ አረዳድ ሰላማዊ ፖለቲካዊ መግባባትን ማደናቀፍ አይኖርብትም ያለው መግለጫው ይህ አካሄድ እንደ ህወሓት ወደ ሰላማዊ ትግል ለመመለስ ለሚዘጋጁ ሀይሎችም ተስፋ የሚያስቆርጥ ተግባር ነው ሲል ገልጾታል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተላለፈውን ውሳኔ የትግራይ አካታች ጊዚያዊ አስተዳደር ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል እና አጠቃላይ የሰላም ሂደቱን የሚያደናቅፍ ተግባር በመሆኑ ቦርዱ ውሳኔውን መርምሮ እንዲያስተካክል ሲል ጥሪውን አቅርቧል።