አዲስ አበባ፣ሰኔ 12፣2014፦የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ ያለው ህወሓት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚደራደር ቡድን መሰየሙን የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በትናንትናው እለት ለኤ.ኤፍ.ፒ ተናገሩ።
ይህ የተባለው የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓት ጋር ስለሚደረገው ድርድር እንዲያጠና የሰየመው ቡድን የመጀመሪያ ስብሰባውን ባደረገ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሆኑን የዜና አውታሩ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመሩት ብልፅግና ፓርቲ የሚደረጉ ድርድሮች በሙሉ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ብቻ እንዲሆን በአፅንዖት መግለፁን ህወሓት ማጣጣሉ ለድርድሩ ሂደት እንደ ፈተና እንደሚታይ ዘገባው አመልክቷል።
የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት “ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቅርበት አላቸው” ሲል ሥጋቱን የገለፀው ቃል አቀባዩ ንግግሩ በኬንያ አስተናጋጅነትና በፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አደራዳሪነት ቢካሄድ እንደሚመርጥ ፍላጎቱን አሳውቋል።
የህወሓት ቃል አቃባይ አቶ ጌታቸው ረዳ “ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያሉበትን ተደራዳሪ ቡድን ወደ ናይሮቢ ለመላክ ዝግጁ እንሆናለን” ሲሉም አክለው ተናግረዋል።
አቶ ጌታቸው “ሁሉንም የድርድር ሂደቶች ለአፍሪካ ኅብረት ማቅረቡ ለኛ እጅግ ኃላፊነት የጎደለው ነገር ይሆንብናል” ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሶ “ንግግሩ በሰላም ጥረት ውስጥ ንቁ ተሣትፎ ያላቸውን ኬንያታን ማሳተፍ ይኖርበታል” ሲሉ አክለው መናገራቸውን አመልክቷል።
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተሰየመው ቡድን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ መሆኑም ነው የተገለፀው።
በግጭቱ የተነሳ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረሃብ ዳርጓቸዋል፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል እና ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የምግብ ዕርዳታ የሚሹ ሆነዋል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።
በመጋቢት መጨረሻ ላይ የተኩስ አቁም ከታወጀ በኋላ ውጊያው የቆመ ቢሆንም ነገር ግን ትግራይ እንደ ኤሌክትሪክ እና የባንክ የመሳሰሉ አስፈላጊ አገልግሎቶችን ማግኘት ባለመቻሏ ከፍተኛ የምግብ እና የነዳጅ እጥረት እንዳለባት የእርዳታ ድርጅቶች ገልፀዋል።
በአማራ እና በትግራይ የባለቤትነት ጥያቄ የሚያነሱበት እና በአሁኑ ጊዜ በአማራ ሃይሎች ቁጥጥር ስር ያለው የምዕራብ ትግራይ ለድርድር አልቀረበም በማለት አቶ ጌታቸው አስረድቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ለህዝብ እንደራሴ ፓርላማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ከ18 ወራት ጦርነት በኋላ በሰሜን ትግራይ ክልል ከሚገኙ አመራሮች ጋር የሰላም ድርድር የሚጀምር ኮሚቴ መቋቋሙን መናገራቸው የሚታወስ ሲሁን ይህ ተደራዳሪ ኮሚቴም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚመራም መናገራቸው የቅርብ ቀን ትውስታ ነው።
ሰኔ 30 ቀን ትኩረቱን በዋነኛነት በዜጎች የጸጥታና ደህንነት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ባደረገው የሕዝብ ተወካዮች የ2014 ዓ.ም 16ተኛው ምክር ቤት የአንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛው መደበኛ በተካሄደው ጉባኤ ላይ የምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በቅርቡ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት በመወሰናቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህወሃት ላይ የሽብርተኝነት ፍረጃውን ሳያነሳ ከሽብር ቡድን ጋር በሰላም አማራጩ ለመወያየት መወሰኑ ወንጀል አይሆንም ወይ ሲሉ ጠይቀው እንደነበር ይታወሳል። ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ “የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሁልጊዜም ለሰላም ቅድሚያ ይሰጣል” ብለዋል።
“ለሰላምም ይሁን ለጦርነት የምንወስነው በብሄራዊ ጥቅማችን ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያን አንድነትና ጥቅሟን በሰላማዊ መንገድ ማስጠበቅ ካልተቻለ የህይወት ዋጋ ከፍለን በመስዋዕትነት ለማስጠበቅ ዝግጁ ነን፡፡ መንግስት በሰላማዊ አማራጭ ተወያይቶ መፍትሔ ለማምጣት መወሰኑ ክፋት የለውም ” ብለዋል። አክለውም መንግስት ስለሰላማዊ አማራጩ ሌሎችን የመብትም ሆነ ሂደቱን በብቸኝነት የመከታተል ሙሉ ስልጣን እንዳለው ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።አስ