ዕለታዊ ዜና፡ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የኢጣሊያን ፖሊስ ተባብረው ለመስራት ተስማሙ


ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ፌደራል

ሐምሌ 15፣ 2014 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፡-የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የኢጣሊያን ፖሊስ በሁለትዮሽና በዓለም አቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በሮም ውይይት በማድረግ የሁለቱ የፖሊስ ተቋማት የጋራ ስጋቶች የሆኑትን ሽብርተኝነትና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ተባብረው ለመከላከል መስማማታቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

በክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የልዑኳን ቡድን ወደ ጣሊያን ሮም ተጉዞ ከጣሊያን ፖሊስ ተቋም ኃላፊ ኮማንደር ጀነራል ቴኦ ሉዚ ጋር ሰፊ ውይይት ከማድረጉም ባሻገር ፖሊስን ለማዘመን በሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችና በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ዙሪያ በትብብር አብሮ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል ሲል ገልፀል።

በውይይቱ ወቅት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአፍሪካ ካሉ ምርጥ አምስት ፖሊስ ተቋማት ተርታ ለመሰለፍ ራዕይ ሰንቆ በከፍተኛ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ክቡር ኮሚሽነር ጀነራሉ ለጣሊያን ፖሊስ ኮማንደር ጀነራል ገልፀው አሁን የደረሰበትን የእድገት ደረጃም ያስረዱ ሲሆን አክለውም በሪፎርም በተሰሩ ስራዎች ወንጀልን በቴክኖሎጂ ታግዞ ለመከላከልና ለመመርመር የሚያስችሉ የፎረንሲክ ምርመራ ላብራቶሪ አደራጅቶ እየሰራ መሆኑንና የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መታጠቁን አንስተዋል።

በአዲሱ መዋቅራዊ አደረጃጀት የቱሪዝም፣ የአቪዬሽን፣ የምድር ባቡር፣ የዩኒቨርስቲ፣ ፈጥኖ ደራሽ እና የኢንዱስትሪ ፖሊስ ማደራጀቱንም አስረድተዋል ። ተቋሙ በአፍሪካ ቀንድ ሮክ (Rock) ከተባለ ድርጅት ጋር ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በተለይም ህገ-ወጥ የሰዎች እና ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም በውይይቱ ወቅት አንስተዋል።

ኮማንደር ጀነራል ቴኦ ሉዚ በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ለብዙ ዘመናት የቆየ መሆኑን ተናግረው ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሁለቱ ፖሊስ ተቋማት በትብብር አብሮ መስራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የጣሊያን ፖሊስ ብቃት ያላቸውን ፖሊሶች በማሰልጠን ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ተቋም በመሆኑ የኢትዮጵያ ፈደራል ፖሊስ ወጣት የፖሊስ መኮንን አመራሮችን አቅም ለማሳደግ ይቻል ዘንድ በጣሊያን ፖሊስ አካዳሚ ገብተው በቴክኖሎጂ፣ በፎረንሲክ ምርመራ እና በፖሊስ ኮማንዶ ሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መውሰድ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተጀመረውን የፎረንሲክ እንዲሁም የዲ.ኤን.ኤ ምርመራ አቅሞችን ለማሳደግ የተለያዩ ቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ስልጠና ድጋፎች ይሰጣሉ ተብሏል። የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ልዑኳን ቡድን የጣሊያን ፖሊስ ኮማንድ ኮንትሮል ሴንተር፣ የፎረንሲክና የዲኤንኤ (DNA) ላብራቶሪን ተዘዋውሮ በመጎብኘት የልምድ ልውውጥ አድርጓል፡፡

 ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.