አዲስ አበባ፣ ህዳር 28/ 2015 ዓ.ም፡- አዲስ አበባ በከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አማካኝነት አምስት አባላት ያሉት የፀረ ሙስና ኮሚቴ መቋቋሙ ከንቲባ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡ የተቋቋመው ኮሚቴ በሀገር ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አማካኝነት ተዋቅሮ ወደ ስራ ከገባው ብሄራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ በተጨማሪ መሆኑም ተገልጧል፡፡
በዚህም መሰረት ወ/ሮ ሊድያ ግርማ የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ፣ አቶ ጀማል ረዲ የአዲስ አበባ ከተማ የፀረ ሙና ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ አቶ ተስፋዬ ደጀኔ የአዲስ አበባ ከተማ የፍትህ ቢሮ ም/ቢሮ ሃላፊ፣ አቶ ጥላሁን ግድየለው የአዲስ አበባ ከተማ አቃቤ ህግ እና ኮ/ር አህመድ መሃመድ የገቢዎች ቢሮ ም/ቢሮ/ሃላፊ የመዲናዋ የፀረ ሙስና ኮሚቴ በመሆን ተመርጠዋል፡፡
እንደ አገርም ይሁን እንደ ከተማ የተጀመረውን የፀረ ሙስና ንቅናቄ ለመግታትና ለማሰናከል በማሰብ ፤ የተለያዩ ደባል አጀንዳዎችን በመፍጠርና በተለይ ትምህርት ቤትን የሁከት ማእከል ለማድረግ በከተማችን የተደራጀ ቡድን እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱን ህዝቡ አውቆ ለኮሚቴው በ 9977 የነፃ የስልክ መስመር አስፈላጊውን ማስረጃና ጥቆማ እንዲያቀርብ የከተማ አስተዳደሩ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
መንግሥት በሙስና ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ የሚያስተባብር፣ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት በተጨማሪ ሌሎችንም ተዋንያን የሚለይና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ማቋቋሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ህዳር 08/2015 ዓ.ም አስታወቀው ነበር፡፡
ኮሚቴ ሰባት አባላት ያሉት ሲሆን፣ እነርሱም፤ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ዶ/ር ጌዴዎን ጢሞቴዎስ፣ አቶ ተክለ ወልድ አጥና፣ አቶ ሰሎሞን ሶቃ፣ አቶ ደበሌ ቃበታ፣ ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ እና አቶ አብዱሃሚድ መሃመድ ናቸው፡፡
ይህን ተከትሎም ከሳምንተ በፊት የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ በክልሉ የሙስና ተግባራት ላይ ክትትልና ምርመራ በማድረግ በሙስና ተግባራት የተሳተፉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ የሚሰራ አምስት አባላት ያሉት የክልሉ የፀረ ሙስና ኮሚቴን ሰይመዋል፡፡
ኮሚቴው በክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ሓጂ ሰመተር የሚመራ ሲሆን የክልሉ ጸረ-ሙስና ሥነምግባር ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የዋና ኦዲት ኃላፊ፣የቅሬታ ሰሚ ኮሚሽን ኮሚሽነርና የክልሉ ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ መካተቱ ተገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስትም በበኩሉ በህዝብና በመንግስት ንብረት ላይ የሙስና ተግባር የሚፈፅሙ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን በማህበራዊ ትስስር ገፁ አስታውቋል፡፡ አክሎም ሙስናን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ በአከባቢው የሚከናወን የሙስና ተግባርን ለመንግስት እንዲጠቁም ጥሪ አቅርቧል፡፡አስ