አዲስ አበባ፣ታህሳስ 14፣2014– የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ ማምሻውን ባደረገው ስብሰባ ከገመገመ በኋላ በአማራ ክልል መንግሥት ከትግራይ ተዋጊዎች ሀይሎች ነጻ ባወጣቸው አካባቢዎች በማኅበረሰቡ፣በአስተዳደር አካላትና በጸጥታ አካላት መወሰድ የሚገባቸውን ተግባራት በመለየት የሚከተሉትን ትእዛዛት ሰጥቷል ።
መንግሥት ከትግራይ ተዋጊዎች ሀይሎች ነጻ ባወጣቸው አካባቢዎች አስተዳደርን መልሶ የማቋቋምና መሠረታዊ የኅብረተሰብ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ያለው እንቅስቃሴ ወጥ በሆነ ሁኔታ እየተተገበረ አለመሆኑን የገመገመው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ በዚህም ምክንያት የጸጥታ ችግሮችና የወንጀል ተግባራት ማኅበረሰቡን እያማረሩት መሆኑን ጠቅሷል፡፡ በመሆኑም የአማራ ክልል መንግሥት የየአካባቢውን አስተዳደር በአስቸኳይ በብቁ አመራሮች እንዲያደራጅ፤ መደበኛ የፖሊስ ኃይሎችም የተጠናከረ ሥራ እንዲጀምሩ እንዲያደርግ፣ እነዚህን ለማድረግ ባልተቻለባቸው ቦታዎች የሚንቀሳቀስ የመከላከያ ኃይል፣ ነጻ በወጡ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ፣ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዙ አዟል፡፡
በተጨማሪም የትግራይ ተዋጊዎች ሀይሎች ተቆጣጥሯቸው በነበሩ አካባቢዎች፣ ባደራጃቸው ሕገ ወጥ መዋቅሮች አማካኝነት፤ የቀደመው አስተዳደር ይጠቀምባቸው የነበሩትን ማኅተሞች በመጠቀምና አዳዲስ ሕገ ወጥ ማኅተሞችን በመቅረጽ ሕገ ወጥ መታወቂያዎችን መስጠቱ፤ የተለያዩ ሕገ ወጥ ሰነዶችን ማዘጋጀቱ ተደርሶበታል ያለው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ በየአካባቢው የተቋቋሙ የመስተዳድር አካላትና የጸጥታ ኃይሎች የትግራይ ተዋጊዎች ሀይሎች ያስቀረጿቸውን ማኅተሞች፣ መታወቂያዎችና ሌሎች ሰነዶች እንዲያመክኑ አዟል ፡፡ በነዚህ አካባቢዎች ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውሮች እንዲሁም የጦር መሣሪያዎች በመኖራቸው ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሥጋት ሊሆኑ የሚችሉ አዝማሚያዎች በመኖራቸው የየአካባቢው ልዩ ኃይልና ፖሊስ በአስቸኳይ እነዚህ ጉዳዮች ሥርዓት እንዲያሲዙ ታዝዘዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ባልተጠናከሩባቸው አካባቢዎችም የመከላከያ ኃይል አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስድ ትእዛዝ ተሰጥቷል፡፡አስ