አዲስ አበባ፣ መስከረም 19/2015 ዓ.ም፡- ገዥዉ ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነዉን ‹ሀገራዊ ምክክር› ልምድ እንድታደርግ በሚል ሃሳብ፣ ፓርቲዉ በበላይነት በሚቆጣጠረዉ የህዝብ ተወካዎች ምክር ቤት ‹ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን› አቋቁሟል፡፡
ከመጀመሪያውም በብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አመሰራረትና ህጋዊነት ላይ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰረታዊ ጥያቄና ተቃዉሞ ገጥሞታል፡፡
በህዳር ወር 2012 ዓ.ም በትግራይ ክልል የተጀመረዉ እና ወደ ሌሎች አጎራባች ክልሎች የተስፋፋዉ የእርስ በርስ ጦርነት የኢትጵያዉያንን ማህበራዊ እሴት የጎዳ፣ ብሔሮችን እርስ በርስ ደም ያቃባ እና ከፍተኛ ዉድመትን ያስከተለ ሲሆን፤ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በእርስ በርስ ጦርነት ምክኒያት በዋነኝነት የተበላሸ የኢኮኖሚ ስርዓት ባላቤት የሆነች፣ ከባድ ድርቅን ጨምሮ ተከታታይ ሀገራዊ አደጋዎች የተጋረጡባት፣ በትንሹ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያወዉያን አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉባት እና በሁሉም ክልሎች ወታደራዊ ጥቃቶች የሚፈፀምባት ሆናለች፡፡
በዚህ መካከል ገዥዉ የብልፅግና ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን የመጀመሪያዉ ፕሬዝዳንት አድርጎ በቅርቡ የመረጠ ሲሆን፤ የስራ አስፈፃሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በማዋቀር ከታቀደዉ “ሀገራዊ ምክክር” ጀርባ ያለዉን አላማ፣ የምስረታ ሂደቱን፣ በፀጥታና በፖለቲካዊ መረጋጋት እና በዜጎች ህይወት ላይ ያለዉን አስተዋፅኦ አንስተዋል፡፡
ለብሔራዊ ምክክሩ የክልሎችን ፍላጎትና ስለቅድመ ዝግጅቶቻቸዉ ኢትዮጵያዉያን “ብሔራዊ ምክክር ምንድን ነዉ?”፣ “ኢትዮጵያ የተረጋጋችና ብቁ ነች?” የሚሉትን ጥያቄዎች ያነሳሉ፡፡
የተለያዩ ምላሾች፣ ጥርጣሬዎችና የህጋዊነት ጥያቄዎች
የአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጠኞች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን ‹በሀገራዊ ምክክሩ› እና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ወሳኝ ጥያቄዎችን በማንሳት አነጋግረዋል፡፡ ሀጋራዊ ምክክር ብቸኛዉ መዳኛ መንገድ መሆኑ ቢነገርም፣ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ቃለመጠይቅ የተደረገላቸዉ መላሾች ምቾት እንደማይሰጣቸዉ ተናግረዋል፡፡
በርካታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሂደቱ ማግለላቸዉን ያሳወቁ ሲሆን፣ ብዙዎች አንደሚስማሙት ሂደቱ በዉዝግብ የታጀበና ፋይዳዉም አጠራጣሪ ነዉ፡፡
ምላሾቹ ከክልል ክልል የሚለያዩ ሲሆን፣ በሃይማትና በብሔርም ተካፋፍሏል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ የሚኖሩ አብዛኞቹ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች ስለ ሂደቱ ብዙም እውቀት የሌላቸው ሲሆኑ፣ በመላ ሀገሪቱ ባሉ ከተሞች የሚኖሩት ግን ሂደቱን የተገነዘቡና የተለያየ አተረጓጎም ያላቸው ይመስላሉ።
በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት ሂሻም ጣሂር እንደሌሎች ሁሉ በሂደቱ ውስጥ ውክልና አለመኖሩን በመግለጽ ውጤቱ እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል።
ሌሎችም የዚሁ ክልል ተወላጆች በወታደራዊ ሃይል ጥቃት የብዙዎች ህይወት መጥፋቱን፣ የሺዎች መፈናቀልን፣ በሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን እና የትግራይ ሃይሎች በአዋሳኝ ከተሞች በመኖራቸው ምክንያት በክልሉ የፀጥታና መረጋጋት እጦት መኖሩን በማንሳት በሂደቱ እና ውጤቱ ላይ ጥርጣሬ ያደረባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከውክልና ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልልም ተመሳሳይ ስጋቶች ተስተጋብተዋል፡፡ በምስራቅ ወለጋ ዞን የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ጃተኒ ገዳ በሂደቱ ህጋዊነት ላይ ጥያቄ ካነሱት መካከል ይገኙበታል፡፡ ጃተኒ እንዲህ ይጠይቃሉ “ይህ ውይይት ከመጀመሪያዉ እንደተረዳሁት ፍትሃዊና ሁሉን አቀፍ ይሆናል ብየ አላምንም፡፡ የችግሩ መንስኤ ራሱ መንግስት ሆኖ ሳለ፣ ችግሩን የፈጠረዉ መንግስት እንዴት ብቻውን ሊፈታው ይችላል?” አክለውም “አስቡት የብሔራዊ ምክክሩ ኮሚሽነሮች የተመረጡት በመንግስት ደጋፊዎችና በራሱ በመንግስት ነው፤ ልንቀበለው አንችልም፣ ምክኒያቱም ሌሎች ቡድኖች እነሱን እና ውሳኔዎቻቸውን አይቀበሉም” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
“ከራስ ጋር ምክክርና የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር ምክክር ፍፁም የተለየ ነው”
ቦኔ ኑረዲን
በኦሮሚያ ክልል መንግስትና በፌዴራል ሃይሎች በአንድ በኩል እና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በሌላ በኩል ስላለው ወታደራዊ ግጭት ጃትኒ አፅንኦት ሰጥተው እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል ተናግረዋል፡፡ “በየቀኑ በደርዘን የሚቆጠሩ ግድያዎች፣ የቤቶች መቃጠል፣ እስራትና መፈናቀል አለ፡፡ በፀጥታ ችግር ምክኒያት ሰብዓዊ እርዳታ እንኳን ለእነዚህ ሰዎች መድረስ አይችልም፡፡ ግጭቱን ለማስቆም ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ምክክሩ ምልክት ብቻ ነው የሚሆነው፤እናም ውጤታማ ወይም የተሳካ ይሆናል ብየ አላምንም፡፡”
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተለያዩ ዞኖች የሚገኙ ነዋሪዎችና ባለሙያዎች ዘንድም ተመሳሳይ አስተያየት ተስምቷል፡፡ በሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ቦኔ ኑረዲን ሂደቱን “መንግስት ከራሱ ጋር ነዉ የሚመክረው” ሲሉ ይገልፁታል፡፡ ቦኔ “ከራስ ጋር ምክክርና የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር ምክክር ፍፁም የተለየ ነው” ብሎ ያምናል፡፡
በሌላ መልኩ አዲስ ስታንዳርድ በአማራ እና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ያነጋገራቸው መላሾች የሰጡት ምላሽ የተለያየ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በአማራ ክልል ደብረ ሲና ከተማ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት አቶ አሸናፊ አንጋሱ ክልሉ በምክክር ሒደቱ አስፈላጊነት ዙሪያ ለማህበረሰቡ የመጀመሪያ ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራቱን የገለፁ ሲሆን፤ አዲስ ስታንዳርድ የአሸናፊን ሃሳብ ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ማረጋገጥ አልቻለም፡፡
ሌሎች ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች መካከል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነው ሲሳይ ግዛቸው በሒደቱ ላይ ያለውን ጥርጣሬ በመግለፅ የፖለቲካ ልሂቃኑ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ አማሮች ላይ ያነጣጠሩ የታጠቁ ሃይሎች እንዲካተቱ ይገፋፋሉ የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡ ሲሳይ በብስጭት “እነዚህ ቡድኖች ሰዎችን ከገደሉና ካፈናቀሉ በኋላ በአንድ ጠረንጴዛ ላይ እንዲቀመጡ መፈቀድ የለበትም፡፡ የሃገሪቱን ማህበራዊ እሴቶች አውድመዋል፣ ለዚህም ዋጋ መክፈል አለባቸው” በማለት ሃሳቡን አካፍሎናል፡፡
የህግ ባላሙያዉ አቶ አብነት ጨምሬ እና በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ነዋሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ታመነ ኢና ሃገሪቱ ዛሬ ከገባችበት ቀዉስ እንድትወጣ ብሔራዊ ምክክር አስፈላጊ መሆኑን ያምናሉ፡፡ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተለይም በወላይታ ዞን ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተገኛኘ ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር ተጨምሮ፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና ባለሙያዎች ተስፋ ቢያደርጉም ለምክክሩ ሒደቱ መሳካት ግን ህዝባዊ ውክልና እና ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል፡፡
አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው ከአዲስ አበባ ውጭ በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች የሚኖሩ ተጠያቂዎች ስለምክክር ሒደቱ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ሲገልፁ፣ በተቃራኒው በመዲናዋ አዲስ አበባ የሚኖሩ ተጠያቂዎች ግን ግንዛቤ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው የግለሰቦች አስተያየት ሙሉ በሙሉ ከመደገፍ፤ ሙሉ በሙሉ ውድቅ እስከማድረግ ይደርሳል፡፡ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የገቡና አስፈላጊነቱን ያመኑ ሃገሮች ብሔራዊ ምክክር በማድረጋቸው አትርፈዋል፡፡ አቶ ሳሙኤል ታደሰ በብሔራዊ ምክከሩ አስፈላጊነት ከሚያምኑት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ “አሜሪካ ከሲቪል መብቶች አብዮት፣ ደቡብ አፍሪካም ከአፓርታይድ ስርዓት በኋላ በነበረው ምክክር አትርፈዋል፤ ኢትዮጵያ ለምን እንደማትችል አይገባኝም” ሲሉ አቶ ሳሙኤል ገልፀዋል፡፡
ከአፋር፣ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ እና ከሶማሌ ክልሎች የተውጣጡ ተጠያቂዎች ግልፀኝነት አለመኖሩን፣ ባላድርሻ አካላት ተሳትፎ አለመኖሩን፣ የአውራ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከውይይቱ መውጣትን፣ በኮሚሽኑ ምስረታ ላይ የመንግስት ጣልቃ ገብነትን እና የአስራ አንዱ ኮሚሽነሮች ምርጫ ቅደም ተከተልን በማንሳት በምክከር ሒደቱ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ገልፀዋል፡፡
“ብሔራዊ ምክክር” ለዘመናት ሲባል የነበረ እና አሁንም ምላሽ ያላገኘ ጉዳይ
የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት የብሔራዊ ምክክር አስፈላጊነት ከሁለት አስርት አመታት በላይ ሲወራበት የነበረ ነው፡፡ በዚህም ታዋቂ ፖለቲከኞች እንደ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና (የወቅቱ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር) እና በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ የነበሩትና አሁን ላይ ኑሯቸውን በውጭ ሃገር ያደረጉት አቶ ልደቱ አያሌው በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ሆኖም መጋቢት 2012 ዓ.ም ሊካሔድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ሃገራዊ ምርጫ ወደ ነሃሴ 2012 ዓ.ም. እንዲራዘም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል አለመግባባት ቢፈጠርም፣ “አካታች ሃገራዊ ምክክር” እንዲደረግ በኢትዮጵየያ አለም አቀፍ አጋሮች የቀረበው ጥሪ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ውሳኔው ለአንድ ወገን ያደላ፣ የሌሎችን ተሳትፎ ከግምት ውስጥ ያላስገባ እና የመንግስት የስልጣን ዘመን ከምርጫ በፊት የሚለቅ መሆኑ እየታወቀ የምርጫ ጊዜውን ማራዘም ምንም አይነት ህገ-መንግስታዊ መነሻ የሌለው ነው በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ እንደ ኦፌኮ ያሉ ፓርቲዎች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሁሉን አቀፍ ምክክር የጠየቁ ሲሆን ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ልደቱ አያሌው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) አካታች የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ጠይቀዋል፡፡
ቢሆንም ገዥው ፓርቲ በምትኩ ፓርላማውን መበተን፣ የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ ህገመንግስቱን ማሻሻል፣ እና የህገመንግስት ትርጓሜዎችን መፈለግ የሚሉ አራት አማራጮችን ያቀረበ ሲሆን፤ ከአራቱ የተሳሳተ ህገመንግስታዊ ትርጓሜን መከተል ለምርጫው አስተማማኝ ጊዜ እስኪፈጠር በሚል ስልጣን ላይ እንዲቀመጥ አስችሎታል፡፡
ምርጫው እንዲራዘም መወሰኑ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የሚመራው የትግራይ ክልል መስከረም 2012 ዓ.ም የአንድ ወገን ምርጫ እንዲያካሒድ እና ህዳር 2012 ዓ.ም በትግራይ ለተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦረነት መነሻ ሆኗል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሃገሪቱ ያሉ ሶስት ታላላቅ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ ከማድረጋቸው በፊት ብቻ ሳይሆን በትግራይ ያለውን ጦርነት እና በሃገሪቱ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ያለዉን ወታደራዊ ብጥብጥ ለማስቆም “ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር” እንዲደረግ ምክረ-ሃሳብ ቢያቀርቡም ገዥው ፓርቲ ሊያምን ባለመቻሉ እነዚህ ፓርቲዎች እራሳቸውን ከምርጫ አግልለዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ኦፌኮ፣ የኦጋደዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) እና ሊቀመንበሩ በቁም እስረኝነት እንዲቆዩ የተደረገበት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ናቸው፡፡
“እነዚህ ቡድኖች ሰዎችን ከገደሉና ካፈናቀሉ በኋላ በአንድ ጠረንጴዛ ላይ እንዲቀመጡ መፈቀድ የለበትም፡፡ የሃገሪቱን ማህበራዊ እሴቶች አውድመዋል፣ ለዚህም ዋጋ መክፈል አለባቸው”
ሲሳይ ግዛቸው
እንደ ባልድራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ያሉ ሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫዉን ሂደት “ከሽፏል” ሲሉ፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋ የአሁኑ ትምህርት ሚኒስቴር ካቢኔ ጉድለቶቹን በማነሳት ሰላምን፣ ሉዓላዊነትንና የሃገር አንድነት ሊጎዳ ይችላል ያሉ ቢሆንም፤ ሁለቱም ሰኔ 2013 ዓ.ም በተካሔደው ሃገራዊ ምርጫ ተሳትፈዋል፡፡
ሁሉም አውራ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያልተሳተፉበት ስድስተኛዉ ሃገራዊ ምርጫ፣ ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ያለተቀናቃኝ አሸናፊ የሆነበትን ለቀጣይ አምስት አመታት እንዲያስተዳድር ጥቅምት 2013 ዓ.ም ፕሬዜዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የስልጣን ዘመኑ አዲስ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡
ሆኖም ምርጫውም ሆነ ውጤቱ ሰላምና መረጋጋትን አላሰገኘም፤ ተጠያቁነትና የኢኮኖሚ ዕድገትም እስካሁን ምላሽ አላገኙም፡፡
ብሔራዊ ምክክሩ እና ብልፅግና
ገዥው ፓርቲ በዋናዋና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃውሞ በታጀበው ምርጫ ስልጣኑን ካፀና በኋላ ብሔራዊ ምክክር እንዲደረግ ሃሳብ አቀረበ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ህዳር 2014 ዓ.ም. የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ኮሚሽን ለማቋቋም የ1265/2014 አዋጅን ሲያፀድቅ በታህሳስ ወር ደግሞ ልዩ ጉባኤ በማካሄድ ለብሔራዊ ምክክሩ ኮሚሽነርነት አስራ አንድ ገለሰቦችን መርጧል፡፡
ልክ እንደምርጫዎቹ ሁሉ ፓርላማው አዋጁን ያወጣበትና አስራ አንዱን ተወያይ ኮሚሽነሮቹን ይፋ ያደረገበት ሂደት ከመጀመሪያው ግልፅነትና አሳታፊነት የጎደለውና የገዢው ፓርቲ የበላይነት የተስተዋለበት ስለነበር እንደገና ከፍተኛ ጥርጣሬ ገጥሞታል፡፡
ዋና ዋና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውይይቱ ሒደት አንሳተፍም ሲሉ እንደገና ተቃውሟቸው ገልፀዋል፡፡ ኦፌኮ የተመራጭ ኮሚሽነሮች ጥቆማ “ፍትሃዊ አልነበረም” ሲል፤ኦብነግ ደግሞ ውክልና የጎደለው ነበር በሏል፡፡ ኦነግ በበኩሉ ስለሂደቱ ምንም እንደማያውቅ ተናግሯል፡፡
“ለምሳሌ መንግስትን ብትወስድ ችግር ፈጣሪ ነው፤ ህወሃት እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎቸን ብትወስድ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሂደቱን እነዚህ አካላት መምራት አይችሉም፤ ሂደቱም ከነዚህ አካላት ነፃ መሆን አለበት”
ራሔል ባፌ
ነገር ን ከፍተኛው ትችት የመጣው ገዢው ፓርቲን ጨምሮ የ53 የአካባቢያዊና አገራዊ ፓርቲዎች ስብስብ ከሆነው የፖሊቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ነበር፡፡ ምክር ቤቱ ፓርላማው አስራአንዱ ተወያይ ኮሚሽነሮቹ ኮሚሽኑን እንዲመሩ ከማፅደቁ አስቀድሞ፤ ፓርላማው ለጊዜው ሂደቱነ አቁሞ የሲቪክ ማህበራትን ጨምሮ ሁሉንም አካላት ያሳተፈ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ አንደገና አንዲያስቀጥል ጠይቆ ነበር፡፡
የፖሊቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (የኢሶዴፓ) አባል የሆኑት ራሔል ባፌ ለአዲስ ስታነዳርድ እነደገለፁት፤ ችግር ፈጣሪዎች መቼም መፍትሔ ሊያመጡ እንደማይችሉ በፅኑ እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡ “ለምሳሌ መንግስትን ብትወስድ ችግር ፈጣሪ ነው፤ ህወሃት እና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎቸን ብትወስድ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሂደቱን እነዚህ አካላት መምራት አይችሉም፤ ሂደቱም ከነዚህ አካላት ነፃ መሆን አለበት” ሲሉም አክለው አስረድተዋል፡፡
የገዢው ፓርቲ ሚዲያዎችን ጨምሮ ለሌሎች መዲያዎች በሰጠቻቸው ቃለመጠይቆች ራሔል ሂደቱ የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጁን ከማውጣት ጀምሮ እስኪፀዲቅና የምክክር ኮሚሽኑን እሰከማቋቋም ብሎም አስራአንዱ ኮሚሽነሮች እሰኪሾሙ ደረስ የነበረው ሂደት ችግር ያለበትና የተጣደፈ እንደነበር ከማጋለጥ ወደ ኋላ አላሉም፡፡
ምክክር በጦረነት ወቀት የሚታሰብ ነውን?
በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ያለው የእርስ በርስ ጦርነት እጅግ ዘግናኝ የሚባል ቢሆንም ቅሉ ይህ ጠ/ሚ አብይ ከመጣ በኋላ ኢትዮጵያን ከገጠማት ችግር ብቸኛው ቸግር አይደለም፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ የተጀመረው ወታደራዊ ጥቃት አሁን ወደ ደቡብ፣ መካከለኛዉና ምስራቅ ኦሮሚያ የተስፋፋ ሲሆን፣ “የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን ስጋት ለእንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋት” በሚል በፌዴራልና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የወሰዱት ወታደራዊ እርምጃ ሌሎች ‹አክራሪ እስላማዊ እንቅስቃሴዎች› እንደነበሩ አሳይቷል፡፡
በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ላይ የመጨረሻዉን ጥቃት ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በዚህ ዓመት መጋቢት 10 እና 12፣ 2022 ዓ.ም. የመጀመሪያ ጉባኤውን ካካሔደ በኋላ በአመራሩ ላይ ለውጥ አድርጓል፡፡ ፓርቲው ጠ/ሚ አብይ አህመድን ፕሬዝዳንት አድርጎ የመረጠ ሲሆን አቶ አደም ፋራህን ከሶማሌ ክልል፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ መርጧል፡፡
አብዲ ሙባረክ እና አብዱልረህዛቅ አህመድ የጎዴና ቀብሪ ዳሃር ከተማ ነዋሪ የሆኑ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ በፓርቲው ጉባዔና በሶማሌ ህዝብ ላይ ያስከተለውን ውጤት አስመልክቶ ከአዲስ ስታንዳርድ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ እያጋጠመው ላለው የሶማሌ ህዝብ ምንም እንደማይሰራ ተናግረዋል፡፡
በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነው አሊ ያሲን ይበልጥ ግልፅ በመሆን ‹በ2010 ከመንግስት ጋር የተስማማናቸው የተሸለ ትምህርት፣ የጤና ስርዓት፣ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎቻችን አልተመለሱልንም፤ ይህ እንዴት የተለየ ሊደርገው እንደሚችል አይታየኝም› ሲል ሃሳቡን አጋርቶናል፡፡
እስካሁን ድረስ የትግራይ ክልልን ጨምሮ ሌሎች ነፍጥ አንስተው ከክልልና ከፌዴራል መንግስት ጋር የሚዋጉ ሃይሎች ለድርድር እንዲቀመጡ የሚገፋፋ ነገር የለም፡፡
“መንግስት ከራሱ ጋር ነዉ የሚመክረው”
ቦኔ ኑረዲን
በሰሜን ኢትዮጵያ እና በኦሮሚያ ያለዉ ጦርነት ከአብይ ኢትዮጵያ በኋላ ያጋጠመ ዋነኛ የፖለቲካ ዉድቀት ሲሆን፣ የአካባቢ ግጭቶች፣ የሃይማኖት፣ የብሔር ግጭቶች ዛሬ በኢትዮጵያ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ከጋምቤላ እስከ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ድረስ የቀን ተቀን ኑሮ ሆኟል፡፡ በአፋርና በሶማሌ ክልል መካከልም የድንበር ግጭት የተለመደ ሆኟል፡፡
በሚያዚያ ወር የመጀመሪያ ሳምንት አካባቢ በተፈጠረው ብጥብጥ በደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ ጂንካ እና አካባቢው ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ዜጎች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ለበርካታ ንብረት መውደምም ምክኒያት ሆኟል፡፡ በዚሁ ክልል በኮንሶ ዞን በተመሳሳይ ወር በተቀሰቀሰ የእርስ በርስ ግጭት ከ10 ቀበሌዎች የተውጣጡ 19000 የሚደርሱ ሴቶችና ልጃገረዶችን ጨምሮ 37000 ለሚጠጉ ዜጎች ‹አዲስ መፈናቀልን› አስከትሏል፡፡ በሰገን ዙሪያ ወረዳ ሚያዚያ ወር ላይ በኮንሶና ደራሼ ማህበረሰብ መካከል በተፈጠረ ግጭት ከ3000 በላይ ዜጎች ከካራት ዙሪያ ወረዳ (ፋቹቻ ቀበሌ) አዲስ ተፈናቅለዋል፡፡ በቦርቃራ፣ ማታራጊዛባ ቀበሌዎች ባለፉት ሳምንታት በተፈጠረ ብጥብጥ ከ1000 በላይ ሰዎች› መፈናቀላቸውን የተመድ ሪፖርት ያመለክታል፡፡
ሚያዚያ 28 በአማራ ክልል ታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ሸክ ከማል ለጋስ በተባሉ የከተማዋ ታዋቂ ሸህ የቀብር ስነስርዓት ላይ በተፈጠረ ጥቃት በርካታ ሙስሊሞች ሲገደሉ፤ ብዙዎች ቆስለዋል፣ መስጊዶች፣ የቅዱስ መፅሃፍ (ቁርዓን) ቅጅዎች እና የሙስሊም የሆኑ የግል ንብረቶች ተቃጥለዋል፡፡
ይህ ሁሉ ሁከትና ብጥብጥ፣ የማህበራዊ እሴቶች መፈራረስ ባለበት በተለይም በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል፤ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ እና በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ተደጋጋሚ ሆነ የእርስ በርስ ግጭት ባለበት “ምክክር በጦረነት ወቀት የሚቻል ነውን ?” የሚለው ጥያቄ መልስ አልተገኘለትም፡፡ አስ
_________________________________________________________________________________//__________________________________________________________
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- ይህ ጽሑፍ ቀደም ሲል በግንቦት 2022 በአዲስ ስታንዳርድ የህትመት መጽሔት ሽፋን ላይ ታትሟል።