ዜና፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውድቅ ያደረገውን በህወሓት ስም ክልላዊ ፓርቲ የመመሥረት ጥያቄ ፍርድ ቤቱ አጸናው

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 1/2015 ዓ.ም፡- የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሚል ስያሜ ፓርቲ ለመመስረት በእነ ገ/ሚካኤል ተስፋዬ በቀረበ የዕውቅና ጥያቄ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውድቅ ማድረጉን በተመለከተ የቀረበለትን ክስ መርምሮ በሰጠው ውሳኔ የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ማጽናቱ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማህበራዊ የትስስር ፌስቡክ ገጹ የፍርድ ቤት ውሳኔውን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ መሰረት ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም  በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተካሄደ ክርክር ህወሓት በሚል ስያሜ የሚጠራ ለረጅም ዓመታት የሚታወቅ ፓርቲ የነበረ በመሆኑ በዚሁ ስም አዲስ ፓርቲ ማቋቋም መራጩን የሚያደናግር በመሆኑ ቦርዱ ያስተላለፈውን ውሳኔ ማጽናቱን አስታውቋል።

የቦርዱ ውሳኔ ስህተት አይደለም ማለቱን አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርዱ ህወሓት ኃይልን መሰረት ባደረገ የአመጽ ተግባር ላይ ሳትፏል በሚል ምክንያት ከህጋዊ የፖለቲካ ፖርቲነት መሰረዙ ይታወሳል። በፌደራልመንግስቱ እና በህወሓት መካከል በፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ  ህወሓት የተሰረዘው ህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ሲል ቢጠይቅም “ለቦርዱ ውሳኔ ምክንያት የሆነው ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጽ ተግባር አሁን ባይኖርም እንደገና ህጋዊ ሰውነቱን ለፖርቲው ለመመለስ የሚያችሉ ድንጋጌዎች በአዋጅ 1662/2011 ተደንግጎ አይገኝም” ሲል ውድቅ እንዳደረገው ይታወቃል። በወቅቱም ህወሓት ህጋዊ ሰውነት የሚያገኘው በድጋሚ ለመመዝገብ ጥያቄ ሲያቀርብ እና ቦርዱ ሲፈቅድ ነው ማለቱም ይታወሳል።

የምርጫ ቦርድን በህወሓት ህጋዊ ሰውነት ዙሪያ ያስተላለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) እና የትግራይ አካታች ጊዚያዊ አስተዳደር በተናጠል ውሳኔውን እንደማይቀበሉት የሚያመላክት መግለጫ ማውጣታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ህወሓት ባወጣው መግለጫ በቦርዱ የተሰጠው ውሳኔ ቅቡልነት የሌለው፣ በፕሪቶርያ የተደረሰው ስምምነትና ህግን መሰረት ያላደረገ ነው ሲል ተችቷል። የፕሪቶርያውን ስምምነት የህዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር-ቤት፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ኣቃቢ ሕግ፣ የክልል መንግስታት እና የከተማ አስተዳደሮች ለስምምነቱ እውቅናና ድጋፍ መስጠታቸውን መግለጫው አውስቷል።

ነገር ግን የምርጫ ቦርድ ስምምነቱን የሚደግፍ ተግባር ሳይሆን የሚያደናቅፍ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ሲል ኮንኗል።  በቦርዱ የተላለለፈው ውሳኔ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት የማይቀበል፣ እየተጠናከረ በመሄድ ላይ ያለውን የሰላም ስምምነቱ ትግበራ ባለቤት አልባ የሚያደርግ፣ ከጦርነቱ ወደ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ለሚገቡ ሃይሎች መደገፍ እና ማበረታታት ሲገባ ድርጅቶችን በማፍረስ ቀጣይ ሰላም እንዳይረጋገጥ የሚያደርግ ነው ብሎ እንደሚያምን አስታውቋል።

በተመሳሳይ የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የሰላም ተስፋ ከመደገፍ ይልቅ የሰላም ስምምነቱ ዋናው ባለቤት የሆነውን ህወሓት ህልውና እንዳይኖረው ለማድረግ ያስተላለፈውን ውሳኔ በሕግም በፖልቲካም ተቀባይነት የለውም ሲል ተችቷል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.