አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17/2015 ዓ.ም፡- የጋምቤላ ክልል ጸጥታ ሁኔታ መደፍረስ በነዋሪዎች ላይ ያደረሰው ከፍተኛ ጉዳት እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የመንግሥትን ተጨማሪ ትኩረት የሚሻ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የጋምቤላ ክልል አካባቢዎች የትጥቅ ግጭቶች፣ የታጠቁ ቡድኖች ጥቃቶችና አጠቃላይ የጸጥታ ችግሮች መስተዋላቸውን ኢሰማኮ በመግለጫው ጠቁሟል።
በክልሉ የሚፈጠሩ ጥቃቶች እና ግጭቶች በአብዛኛው ብሔር ተኮር መሆናቸውን አመላክቷል። በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ መንደሮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መውደማቸውን ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ አስታውቋል።
በተለይም ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ላለው የጸጥታ ችግር መነሻ፣ በኢታንግ ልዩ ወረዳ በተወሰኑ ነዋሪዎች መካከል የተነሳ አለመግባባት መሆኑ ያስታወቀው ኮሚሽኑ ይሄው አለመግባባት በፍጥነት ወደ ብሔርን መሠረት ያደረገ ውጥረት እንደተሸጋገረ እና ወደ ለየለት ግጭት ማምራቱን ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ አመላክቷል።
የተለያየ ብሔር ታጠቂ ቡድኖች በኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ ጋምቤላ ወረዳ፣ ጎግ ወረዳ፣ በጋምቤላ ከተማ ብሔር ብሔረሰቦች ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እና በከተማው በሚገኙ ሌሎች ሰፈሮች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን እና በዚህም ምክንያት በርካታ ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና ንብረት ውድመት መድረሱን ጠቁሟል።
ከሁለት ወራት በላይ ለዘለቀው የጋምቤላ ክልል የጸጥታ ችግር ዋና ተዋናዮች የክልሉ ኑዌር ብሔረሰብ ታጣቂዎች፣ የአኝዋ ብሔረሰብ ታጣቂዎች፣ ከጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን የመጡ ታጣቂዎች እና በአንዳንድ የስደተኛ ካምፖች ውስጥ እንደሚኖሩ ስደተኞች መሆናቸውንም ኢሰማኮ በመግለጫው አካቷል።
በሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. እና ቀደም ብሎ ባሉት ቀናቶች በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ነዋሪዎች በደረሰባቸው ሥጋት ሳቢያ የጋምቤላ ከተማ መደበኛ እንቅስቃሴ ቀንሶ፣ ብሎም ተቋርጦ መቆየቱን የገለጸው ኢሰማኮ የክልሉ መንግሥት ከሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ላልተወሰኑ ቀናት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተፈጻሚ የሚሆን የሰዓት እላፊ ገደብ፣ እንዲሁም ከተመደቡ የጸጥታ አካላት ውጪ መሣሪያ ይዞ የመንቀሳቀስ ገደብ መጣሉን አውስቷል።
ሆኖም በክልሉ የተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ አፈጻጸም ነዋሪዎችን ለተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይዳርግ መከላከልን ጨምሮ፣ በክልሉ በተለያየ ወቅት የሚያገረሹ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ነዋሪዎችን ለከፍተኛ ጉዳት የዳረጉ ጥቃቶችን እና ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም ተጨማሪ ትኩረት እና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ አሳስቧል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ይህንኑ ተግባር ለመደገፍ እና በተለይም በነዋሪዎች እና በክልሉ በተጠለሉ ስደተኛ ካምፖች ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ከነዋሪዎች፣ ከስደተኞች ተወካዮች፣ ከተቀባይ ማኀበረሰብ ተወካዮች፣ ከፌዴራል እና ጋምቤላ ክልል ጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም በስደተኞች አያያዝ ላይ ከሚሠሩ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች የተውጣጣ ጊዜያዊ አስተባባሪ የሥራ ቡድን ማዋቀር ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚኖረው” መሆኑን መግለጻቸውን አስታውቋል። አስ