ዜና፡ ፖሊስ በልመና ለተሰማሩ ሰዎች ገንዘብ የሚሰጡ እና ግብይት የሚፈፅሙ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ገለፀ

ረዳት ኮሚሽነር ሸዋይርጋ ግዛው፣ ፎቶ የአዲስ አበባ ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2015 ዓ.ም፡- በትራፊክ መብራቶች እና በመስቀለኛ መንገዶች ላይ የሚከናወኑ ህገ-ወጥ ንግድ እና የልመና ተግባራት ላይ በተሰማሩ ግለሰቦችና ገንዘብ በሚሰጡና በሚገበያዩ አሽከርካሪዎች ላይ በህጉ መሠረት ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ፡፡

በመንገዶች ላይ የሚከናወኑ ህገ-ወጥ ንግድ እና የልመና ተግባራት እንዲሁም የአሽከርካሪዎች ደንብ አክባሪ አለመሆን ለትራፊክ አደጋ መጨመር ምክንያት ሆኗል ያለው ፖሊስ በልመና ለተሰማሩ ሰዎች ገንዘብ የሚሰጡ እና ግብይት የሚፈፅሙ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡

በዚህ ተግባር የትራፊክ መብራቶች ባሉባቸው ጎዳናዎች የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች የሚፈፀምባቸው ቦታዎች እየሆኑ መምጣታቸው ተፈገልጧል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሸዋይርጋ ግዛው እንዳሉት ትራፊክ ፖሊሶች በቁጥጥር እና በማስተናበር ስራ ላይ በሚያተኩሩበት ወቅት በትራፊክ መብራት እና በመስቀለኛ መንገድ ላይ በልመና እና በህገ ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች መሃል መንገድ ድረስ በመግባት ለትራፊክ ፍሰቱ እንቅፋት እየሆኑ እና ራሳቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ይገኛሉ፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ ለእነዚህ ሰዎች ገንዘብ በሚሰጡ እና ግብይት በሚፈፅሙ አሽከርካሪዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር እና የሚወሰደው እርምጃ አጥጋቢ ነው ባይባልም የችግሩን መስፋት እና መልኩን መቀየሩን ተከትሎ በቀጣይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ረዳት ኮሚሽነር ሸዋይርጋ ግዛው አስረድተዋል፡፡

በሚኒስትሮች ምክርቤት የወጣው የትራንስፖርት መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 395/2009 በትራፊክ መብራት ላይ ወይም በመስቀለኛ መንገድ ላይ በልመና ተግባር ለተሰማሩ ሰዎች ገንዘብ የሰጠ ወይም ግብይት የፈፀመ አሽከርካሪ ቅጣት እንደሚጣልበት ይደነግጋል፡፡

ስለሆነም ህብረተሰቡ በተለይም አሽከርካሪዎች በትራፊክ መብራት ላይ የሚደረግ ልመና እና ህገ ወጥ ንግድ ለአደጋ አጋላጭ መሆኑን ተገንዘበው ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ እና ባለድርሻ አካለትም በትራፊክ መብራት አካባቢ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ህጋዊ ኃላፊነታቸው እንዲወጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪዉን አስተላልፏል፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.