ጥልቅ ትንታኔ፡ ከጦርነቱ በኋላ የትግራይ ክልል ፖለቲካ ምህዳር ምን ገፅታ ይኖረዋል? ቀጣዩ የትግራይ የፖለቲካ ትግል አቅጣጫ ምን ይሆን?

በሚሊዮን በየነ @MillionBeyene

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 26/2015 ዓ.ም፡- በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙ ይታወቃል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ቆይታ ቢያንስ ስድስት ወራት ቢበዛ ደግሞ አንድ አመት እንደሚሆን ተደንግጓል። ይህም ማለት ግዜው ሲያልቅ በክልሉ ምርጫ ይካሄዳል ማለት ነው። ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የስልጣን ግዜ ማብቃት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ አሸናፊ ሆኖ ማን ክልሉን ያስተዳድር ይሆን ተብሎ ለሚቀርብ ጥያቄ ምላሹ የሚያሳስባቸው በርካቶች ናቸው።

ላለፉት ሰላሳ እና ከዚያ በላይ ዓመታት ክልሉ ሲተዳደር የኖረው በአንድ ፓርቲ ማለትም በህወሓት ብቻ ነው። ህወሓት አምባገነንነት የተጠናወተው ፓርቲ በመሆኑ በቀጣዩ በክልሉ በሚካሄደው ምርጫ እንደተለመደው የፖለቲካ ምህዳሩን አጥብቦ ስልጣኑን በመቆጣጠር መቀጠል ይፈልጋል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ በክልሉ ተከስቶ ከፍተኛ ውድመት ባደረሰው ጦርነት ሳቢያ ነገሮች ተቀይረዋል የሚሉም አሉ።

በግዚያዊ አስተዳደር ውስጥ የተካተተው የባይቶና ትግራይ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጸጋዘአብ ካህሱ በትግራይ ሙሉ በሙሉ የፖለቲካ ምህዳሩ ተቀይሯል የሚል እምነት ፓርቲያቸው እንዳለው አስታውቀው ይህ ማለት አሁን ትግራይ ውስጥ ከብዝሃ-ፓርቲ ስርዓት፣ ከዲሞክራሲ ሂደት ውጭ ልክ እንደ ድሮ በአንድ ፓርቲ ስርዓት በአምባገነንነት መቀጠል አያስችልም፤ ያ ምህዳር የለም፣ ተኗል ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

ህወሓት ትግራይን ለ30 እና ከዚያ በላይ አመታት የራሱ ንብረት አድርጓት ነበር የኖረው ያሉት ዶ/ር ጸጋዘአብ ህወሓት ከእኔ ማዕቀፍ ውጭ ሌላ አያስፈልግም በሚል ነበር አፍኖ ክልሉን ይመራ ነበር ሲሉ አውስተው ያሳለፍናቸው እና የመጣንበት መንገድ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት አስገዳጅ ሁነቶች ናቸው ሲሉ አመላክተዋል።

እንደ ባይቶናው ሊቀመንበር ሀሳብ ከሆነ ሌላው ምህዳሩን የሚያስገድደው ደግሞ በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደሩ በተግባር ከህወሓት እጅ መውጣቱ ነው ሲሉ ይገልጻሉ። ይህንንም ሲያብራሩ ህወሓት ፈልጎት ሳይሆን ተገዶ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ ስልጣን ማጋራቱን ጠቅሰው ከተጠቀምንበት እድሉ ተፈጥሯል ብለዋል።

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንሰና ስትራቴጂ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህሩ ገ/መድህን ገ/ሚካኤል በበኩላቸው በትግራይ የፖለቲካ ምህዳሩ በትክክል አና በእርግጠኝነት ይሰፋል ብለን ለመናገር እንዳንችል ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉም በጊዜያዊ አስተዳደሩ አለመሳተፋቸው እንቅፋት ሁኗል ሲሉ ገልጸዋል። ሁሉም የትግራይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሰጣቸውን ቦታ ተቀብለው ገብተው ቢሆን የፖለቲካ ምህዳሩ ላይመለስ እንዲሰፋ ያደርገው ነበር ብቻ ሳይሆን ወደ ብዝሃ ፓርቲ ለማምራት እና ወደ አሃዳዊ ፓርቲ ላለመመለስ የሚኖረው አስተዋጽኦ እጅግ ብዙ ነበር ብለዋል።

የታሪክ ሙሁር እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ ጸጋዘአብ ካሳ ግን በሁለቱም አይስማሙም። ክልሉን ለበርካታ አመታት ሲያስተዳድር የነበረው ህወሓትም ሆነ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በክልሉ እያራመዱት ያለው ፖለቲካ ቅርጽ አልባ ሆኗል ሲሉ ተችተው ግለሰቦች የሚዘውሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች እየፈለጉ ነው፤ የራሳቸው የሆነ አጀንዳ መያዝ ያልቻሉ የሌሎች ፓርቲዎች (ከክልሉ ውጭ ያሉ) አጀንዳ ማስፈጸም ላይ ያተኮሩ ብቻ ሆነዋል ብለዋል። በፓርቲዎቹ ውስጥም የፖለቲካ ሽኩቻ እና ክፍፍል እየበዛ መምጣቱን የጠቆሙት አቶ ጸጋዘአብ ካሳ በራሳቸው ፍላጎት አቋም ኖሯቸው እየተንቀሳቀሱ አይደለም ሲሉ ኮንነዋል። የሚወክሉትን ማህበረሰብ አቋም ግልጽ በሆነ መልኩ አሳውቀው መንቀሳቀስ የሚችሉ ፓርቲዎች የሚጠይቅ ምህዳር ነው ያለው፣ ያን መሆን መቻል ይጠይቃል ሲሉ ገልጸዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ የግዜ ገደብ ማብቂያና ምርጫ ማከናወን ጉዳይ

ጊዜያዊ አስተዳደሩ የስልጣን ግዜ ቢበዛ በአንድ አመት እንደሚሆን የተገለፀው ይቻል ይሆን የሚል ጥያቄ አንስተን ለባይቶናው ሊቀመንበር ዶ/ር ጸጋዘአብ ካህሱ ጠይቅናቸው፤ እሳቸውም፣ በዚህ ግዜ ገደብ ውስጥ ሁሉም ነገር ይጠናቀቃል የሚል እምነት የለንም በማለት መልስ ሰጥተዋል። በትግራይ ያለው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መዋቅር መፍረስ አንዱ ምክኒያት መሆኑንም ነው የገለፁት። ምርጫ ቦርድ እስካሁን ምንም አይነት እንቅስቃሴ እያከናወነ አለመሆኑን ጠቁመው፤ በየ ወረዳው እና ዞን ቢሮዎች ተከፍቶ፣ በሰው ሀይል ተጠናክሮ፣ የመራጮች ምዝገባ ተደርጎ ምርጫውን ለሚያሸንፍ አካል ስልጣን ማስረከብ በአንድ አመት ግዜ ውስጥ መከናወን ይችላል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ ያሉት የፖለቲካ ጥያቄዎች ተፈትተው ዲሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ ይካሄዳል የሚል እምነት የለንም ብለዋል። ሜዳውን ማመቻቸት በአንድ አመት ግዜ ውስጥ የሚቻል አይመስለንም ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንሰና ስትራቴጂ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህሩ ገ/መድህን ገ/ሚካኤል እና የታሪክ ሙሁር እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ ጸጋዘአብ ካሳ ግን ይቻላል የሚል እምነት አላቸው።

መምህር ገ/መድህን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋነኛ ስራ ምርጫውን ማመቻቸት መሆኑን ጠቁመው ምርጫ ቦርድ በትግራይ ምርጫ ለማድረግ ከሚያስፈልገው ግዜ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በደንብ ተደራጅተው፣ ያላቸውን የህግ ክፍተት አሟልተው ለምርጫው ዝግጁ የሚሆኑበት ሁኔታ ለመፍጠር አንድ አመት በቂ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

ዝግጅት ማድረገን በተመለከተ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጅት የሚጠናቀቅ ነው የሚል እምነት የለኝም ያሉት ገ/መድህን ገ/ሚካኤል እንኳን ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ህውሓትም ያለቀ ዝግጅት ይኖረዋል ብየ አላምንም፣ ሂደት ነው። ከነጉድለቶቻቸው መቅረብ ይችላሉ። አንድ አመት ለልማት እና መልሶ መገንባት አጭር ሊሆን ይችላል፣ ምርጫ ለማካሄድ ግን ከታሰበበት እና ከተሰራበት ያንሳል ብየ አላምንም ብለዋል። 

አቶ ጸጋዘአብ ካሳ በበኩላቸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ በአንድ አመት ውስጥ ምርጫ አከናውኖ ስልጣን ለማስረከብ የሚችለው የሰላም ስምምነቱ አተገባበርን ተንተርሶ መሆኑን አስታውቀው የሰላም ስምምነቱ በትክክል በተያዘለት ግዜ እየተተገበረ ከሄደ ምርጫ ማካሄዱ የመሳካት እድል ይኖረዋል ብለዋል።

ቀጣዩ የትግራይ የፖለቲካ ትግል አቅጣጫ

ኢትዮጵያ እንደሀገር ትግራይ እንደ ክልል ከጦርነት አዙሪት ወጥተው እፎይ ያሉበት ዘመን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የአስራ ሰባት አመቱ የትጥቅ ትግል ሲወሳ በአስር ሺዎች የትግራይ ወጣቶች መስዋእት መሆናቸው ይታወሳል። ያሁኑ ይባስ፣ ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ሀይሎች መካከል የጠፋው የሰው ህይዎች ከአስር እጥፍ በላይ መሆኑ ተገልጿል። ከዚህ በኋላስ? የትግሉ አቅጣጫ ምን ይሆን ስንል ጠየቅን፡፡

በግልጽ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እየገባን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ሲሉ የገለጹልን ዶ/ር ጸጋዘአብ ባይቶና ይህን ነገር መቀበሉን ገልጸው ለዚህም ነው የጊዜያዊ አስተዳደሩ አካል ሆነን ለመቀጠል የወሰነው እና የተቀበልነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።  ዝግጅታችን ይሄን መሰረት ያደረገ ነው ያሉት ጸጋዘአብ ካህሱ በሰላማዊ ትግል ህወሓትን መቶ በመቶ አሸንፎ ስልጣን መረከብ ይቻላል፣ ምርጫ ላይ እንዲሁ ለመሳተፍ ወይንም የዲሞክራሲ እንቅስቃሴን ለማገዝ አይደለም ዝግጅታችን፤ በምርጫው የምንሳተፈው አብላጫ ድምጽ አግኝተን ትግራይን ለማስተዳደር ነው፤ አሁን በትግራይ ያለው አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ነው ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተውናል።

ህወሓት ባለመደው እና በማያውቀው መንገድ ነው የምንገጥመው ያሉት የባይቶናው ጸጋዘአብ ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መተባበር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በጥቃቅን ልዩነቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በመተማመን በጋራ ሊንቀሳቀሱ ይገባል ሲሉ አሳስበው በቀጣይ የትግራይ ምርጫ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ አላማ የሚሰባሰቡበት መንገድ ማመቻቸት አለባቸው፤ ባይቶና ይህንን ለማሰባሰብ እና ለመምራት ዝግጁ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት ባይቶና ከአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ግንባር ስለመመስረት እና እስከ ውህደት ድረስ ለመሄድ የሚያስችል ውሳኔ በማዕከላዊ ኮሚቴው ማስወሰኑንም ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል።

የመቀለ ዩኒቨርስቲ መምህሩ ገ/መድህን ገ/ሚካኤል በበኩላቸው የሰላማዊ ትግል ልምምድ እንደ ሀገር በጠቅላላ እንዲሁም እንደክልል ካየነው የለም ማለት እንደሚቻል አመላክተው በጊዜያዊ አስተዳደሩ የትግራይ ተፎካካሪ ሀይሎች ከእነችግሩም ቢሆን የተሰጣቸውን ቦታ አለመቀበላቸው እና አለመካተታቸው የዚህ ውጤት መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ሀገርም ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝቡ ድምጽ የሚሰጣቸው ገዢውን ፓርቲ ለመቃወም፣ ቅሬታውን ለመግለጽ እንጁ ስልጣን ቢይዙ፣ ሃላፊነት ቢሰጣቸው እንደሚሰሩ ሳይጠራጠር በማመን አለመሆኑን ጠቁመው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህንን እውነታ  መቀበል አልቻሉም ሲሉ ተችተዋል። ተቃዋሚ ማለት ስልጣን መያዝ ይችላል፣ ሃላፊነት ሊወጣ ይችላል የሚለውን አረዳድና መንፈስ በህዝቡ ላይ አይታይም፣ አልሰፈነም ሲሉ ገልጸዋል።ፓርቲዎቹ በዚህ ደረጃ እየተዘጋጁ ባለመሆኑ ነው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ ለመሳተፍ ድፍረት ያጡት፤ ተቀብለው እና ተሳትፈው ቢሆን ኑሮ እንደ ዝግጅት ሊጠቀሙበት በቻሉ ነበር የሚል እምነት አለኝ ብለዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.