ዜና: የአማራ ክልል የፌዴራል መንግስት የያዘውን የድርድር አቋም ይደግፋል፤ የህወሃት ሃይል ሰሜን ጎንደር፣ ዋግ ኽምራና ቆቦ አካባቢዎችን እስካሁን ድረስ ተቆጣጥሯል- ርእሰ መስተዳድሩ

ዶክተር አኒቲ ዌበር እና ዶክተር ይልቃል ከፋለ ምሰል: አሚኮ


አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21/2014 ዓ.ም፡- የአማራ ክልል ከህውሃት ጋር ያጋጠመውን ጦርነት በሰላም አማራጭ ለመፍታት የፌዴራል መንግስት የያዘውን አቋም የክልሉ መንግስትና ህዝቡ እንደሚድግፉት የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ

የህወሃት ሃይል በአማራ ህዝብ ላይ አለም አቀፍ ወንጀል ፈፅሟል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ “ንፁሃንን በጅምላ በመግደል፣ ሴቶችን በመድፈር፣ ማህበራዊ ተቋማትን ጨምሮ ሃብትና ንብረት በመዝረፍና በማውደም አሳዛኝ ድርጊት ፈፅሟል” ብለዋል። አክለውም የህወሃት ሃይል በሰሜን ጎንደር፣ ዋግ ኽምራና ቆቦ አካባቢዎችን እስካሁን ድረስ በወረራ በመያዝ ህዝቡ የምግብ፣ የህክምናና ሌሎች ሰብአዊ ድጋፍ እንዳያገኝ በማድረግ አሰቃቂ ግፍ እየፈፀመ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከአውሮፓ ህብረት የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ዶክተር አኒቲ ዌበር ጋር በጽሕፈት ቤታቸው በተወያዩበት   ወቅት እንዳሉት፤  የህወሃት ሃይል ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት በመፈፀም ዜጎችን ለመከራና ስቃይ ቢዳርግም ለመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል። የተፈጠሩትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ውይይትና ንግግር አስፈላጊ በመሆኑ “ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን እንገኛለን” ብለዋል። አክለውም ይሁን እንጅ የህወሃት ሃይል ፍላጎቱን በሀይል ለመጫን ከመጣር ውጪ ለሰላም ፍላጎት እንደሌለው እየፈፀመ ካለው ድርጊት ተገንዝበናል ሲሉም ለልዩ መልዕክተኛዋ አስረድተዋል።

የአውሮፓ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልእክተኛ ዶክተር አንቲ ዌበር በበኩላቸው ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር በውይይት በመፍታት አንድነቷን አጠናክራ ለማስቀጠል የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ጠቅስው የአውሮፓ ህብረት ለአማራ፣ ትግራይ፣ ሶማሌና ሌሎች ችግር ለገጠማቸው ክልሎች ሰብአዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

መልእክተኛዋ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያላት ተፅእኖ ቀላል እንዳልሆነ ገልፀው የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። በተጨማሪም የአማራ ክልል መንግስትም ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በማድነቅ ለሰላም አብረው እንደሚሰሩ ልዩ መልክተኛዋ አስታውቀዋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.