ዜና፦ ኢትዮጵያ ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደታገደ መቆየቱን አስተባበለች፤ ዕርዳታ “ከምን ጊዜዉም በተሻለ ሁኔታ እየገባ ነዉ” አለች

አዲስ አበባ፡ ሕዳር 2 ፣ 2015፦የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በፕሪቶሪያ በተደረሰው ስምምነት መሠረት የሰብዓዊ ዕርዳታ በአስቸኳይ እና ያለገደብ ወደ ትግራይ እንዲገባ በማለት የሰጠውን መግለጫ ተከትሎ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን “እስካሁንም በመከላከያ ወዳልተያዙት አካባቢዎች ጨምሮ ዕርዳታ ከምንጊዜዉም በተሻለ ሁኔታ [ወደ ትግራይ] እየገባ ነዉ” አሉ።

አክለዉም 70 በመቶ የትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መሆኑን ገልጸዋል።

አምባሳደር ሬድዋን “35 ምግብ የጫኑ እንዲሁም ሶስት መድሃኒት የጫኑ የጭነት መኪናዎች ሽሬ ከተማ ደርሰዋል፤ በረራዎች ተፈቅደዋል፤ ተቋርጠዉ የነበሩ አገልግሎቶች እንደገና እየተጀመሩ ነው” ብለዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በትዊተር ገፁ ባወጣው መግለጫ አምባሳደር ሬድዋን በናይሮቢ “በሳምንቱ መጨረሻ የሰብአዊ ዕርዳታ በፕሪቶሪያ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ያለ ምንም እገዳ ይሰራጫል። በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች የሚገኙ ችግር ዉስጥ ኢትዮጵያውያን እርዳታ ይደርሳቸዋል” ማለታቸዉን ጠቅሷል።

ቢሮው “የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ነበረበት መመለስ፣ የዜጎች ጥበቃ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ስራ” እንዲሁም “ስምምነቱን አክብሮ ተግባራዊ የማድረግ እርምጃዎችን እየጠበቀ መሆኑን” ተናግሯል። አምባሳደር ሬድዋን ለመግለጫዉ በሰጡት ምላሽ “ስምምነቱ ተቋርጠዉ የነበሩ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ እድል ፈጥሯል፡ ዕርዳታ ማድረስ ላይም ምንም አይነት እገዳ የለም” ብለዋል።

ይህ የሆነዉ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የሰላም ስምምነት ቢፈረምም አስቸኳይ እርዳታ እስካሁን ወደ ትግራይ እንዲገባ አልተደረገም ካለ ከአንድ ቀን በኋላ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ አደጋ ዳይሬክተር ሚካኤል ራያን ረቡዕ ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት “በትግራይ ውስጥ ያሉ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ አፋጣኝ ፣ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል

ዛሬ ማለዳ በመቀሌ የሚገኘው የአይደር ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ክብሮም ገብረስላሴ እንደተናገሩት “ስምምነቱ ከተፈረመ ከዘጠኝ ቀናት በኋላም ህሙማን እንደ ኢንሱሊን እና አንቲባዮቲኮች ባሉ መሰረታዊ መድሃኒቶች እጦት እየተሰቃዩ ይገኛሉ” በማለት በቲዊተር ግፃቸዉ ፅፈዋል።

በኬንያ ናይሮቢ በፌዴራል መንግስት እና በትግራይ ባለስልጣናት መካከል የሚደረገው ውይይት የቀጠለ ሲሆን የትግራይ ታጣቂዎችን የማስፈታት እና የሰብዓዊ ዕርዳታ ዋና አጀንዳዎች እንደሆኑ ተዘግቧል።

በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው የጦርነት ማቆም ስምምነት አንቀፅ 5 “የኢፌዲሪ መንግስት የሴቶች፣ ህፃናት እና አረጋዊያንን ጨምሮ የተጋላጭ ወገኖችን ልዩ ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን ያፋጥናል” ይላል።

አክሎም በአንቀጽ 11 ላይ የስምምነቱን አፈፃፀም የሚከታተል የጋራ ኮሚቴ ለማቋቋም ሁለቱም አካላት መስማማታቸዉን ይገልፃል። ይሁን እንጂ ይህ የዚህ የጋራ ኮሚቴ ስለመቋቋሙ እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም።

በተያያዘ ዜና የትግራዩ ከፍተኛ ባለስልጣን ክንደያ ገብረህይወት ሃሙስ እለት በትዊተር ገፃቸው ላይ እንዳስታወቁት ስምምነቱ ቢደረግም የኤርትራ ወታደሮች ሰላማዊ ዜጎችን መግደላቸውን እና በሽሬ እና አዲ ዳዕሮ ከተሞች አከባቢ የአየር ድብደባ እየፈፀሙ መሆኑን ገልፃዋል።

“የኤርትራ ሃይሎች በሽሬ እና አዲ ዳዕሮ ዙሪያ ግድያ፣ አፈና እና የአየር ድብደባ መፈፀም ቀጥሏል። ዛሬ ሽሬ ላይ እንደታየው ሴቶችን ጨምሮ የኤርትራ ሰላማዊ ሰዎች በዘረፋ ተሰማርተዋል” ብሏል።

በኬንያ ናይሮቢ እየተካሄደ ባለው የፌደራል እና የትግራይ ጦር ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች መካከል እየተካሄደ ሲሆን ስብሰባዉ ያለፈው ዕሮብ ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም፣ መራዘሙን ዘገባዎች አመልክተዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.