ዜና፥ ኢዜማ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ገብነቱን እንዲያቖም ጠየቀ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ

አዲስ አበባ፣ጥር 22/ 2015 ዓ.ም፡– የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ(ኢዜማ) መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ገብነቱን እንዲያቖም ጠየቀ። “ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተፈጠረውን ችግር በአንክሮ ሲከታተል ቆይቷል” ያለው ኢዜማ፤ “የተለያዩ የፖለቲካ ዓላማ ያነገቡ ግለሰቦችም ሆኑ ሌሎች ቡድኖች በተፈጠረው ችግር ውስጥ የሚያደርጉት ተሳትፎ ችግሩን አባብሰው ደም አፋሳሽ ግጭት ሊያስከትሉ የሚችሉ አዝማሚያዎች እየተስተዋሉ በመሆኑ፤ መንግሥት ራሱን ጨምሮ ሌሎች የአደጋ ስጋት ምንጮችን ገምግሞ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ እናሳስባለን” በማለት አክሏል።

ከዚህም በተጨማሪም ፓርቲው በኢትዮጵያ የሚገኙ የዕምነት ተቋማት “የማኅበረሰቡን እሴት በመገንባት የሚውስዱት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ያምናል” የሚለው ኢዜማ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህሕዶ ቤተክርስቲያንም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነች”በማለት አክሎ ገልጿል። ይሁንና፥ “ኢትዮጵያ አሁን ላይ እየተዳደረችበት ባለው ሕገ መንግሥት አንቀፅ 11 ላይ በግልጽ እንደሰፈረው መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው። መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ብሎ ከደነገገው በተቃራኒ የፀጥታ ኃይሎች እየወሰዱት ያለው እርምጃ አሳስቦናል” በማለት ፓርቲው ተናግሯል።

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የውስጥ ጉዳይ ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተስተዋሉ ያሉ ጣልቃ ገብነቶች መዘዛቸው ከባድ መሆኑን ተረድቶ በአስቸኳይ ሕግ እና ሥርዓትን አክብሮ እንዲያስከብር እንጠይቃለን።

የሃይማኖት ተቋማት ላይ በማናቸውም ወገን የሚደረግ ጣልቃ ገብነት መዘዙ ብዙ ስለሆነ፤ ከመንግስት በተጨማሪም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሲል ኢዜማ ጨምሮ አሳስቧል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.