ዜና፡ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት በክልል አደረጃጀት ጉዳይ ላይ የሚጠብቀው የፌደሬሽን ምክር ቤት መልስ መሆኑ ተነገረ




ምንጭ፡ ጉራጌ ሚዲያ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 27፣ 2014 ዓ.ም ፦የጉራጌ ዞን ምክር ቤት እስከ አሁን ድረስ የክልል አደረጃጀት ጉዳይን በአጀንዳነት እንዳልያዘ እና ጉባኤው የሚያካሄድበት ቀን እንዳልተቆረጠም የምክር ቤቱ የኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዓለምይርጋ ገለፁ፡፡

እንደ አቶ ዓለምይርጋ አነጋገር የጉራጌ ዞንን በክልል የማደራጀት ጥያቄ ረዥም አመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ይህ የሕዝብ ጥያቄ እንደመሆኑ መጠን ምክር ቤቱ ለተፈፃሚነቱ ይሰራል ብለዋል፡፡

ከሳምንት በፊት በጉዳዩ ላይ በተለያ ደረጃዎች መንግሥት ማወያየቱን አስታውሰው፣  “ሕዝቡ ምክር ቤቱ ያፀደቀውን በመጠባበቅ ላይ ነው፤ የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ይመለስልኝ የሚል አቋሙን አሰምቷል” ብለዋል፡፡

በመሆኑም ምክር ቤቱ የሕዝቡን ጥያቄ ከማስፈፀም ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም ያሉ ሲሆን አክለውም የምክር ቤቱ አባላት ተገዢነታቸው ለሕገ- መንግሥት፣ ለሕዝቡ እና ለሕሊናቸው ብቻ መሆኑን አስታውሰው ያለማንም ተፅዕኖ የሕዝቡን ውሳኔ የሚያስፈፅም ምክር ቤት ያላቸው መሆኑን አቶ ዓለምይርጋ  ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ክልል የሚገኙ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች አንድ ላይ በመደራጀት ሁለት የተለያዩ ክልሎች ለመመስረት በየምክር ቤታቸው ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቧ ይታወቃል።  የጎፋ ዞን ህዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 9ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤውን እና የስልጤ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 22ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የክልል አደረጃጀትን በተመለከተ በደቡብ ክልል ከሚገኙ ከሌሎች አጎራባች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር አብሮ ለመደራጀት የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ  ሁለቱም ምክር ቤቶች አፅድቀዋል።

በዚህም መሰረት በአዲስ የክልል አደረጃጀት በጋራ ለሚደራጁ 11 መዋቅሮች ማለትም ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ ዞኖች እና አማሮ፣ አሌ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ እና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች መሆናቸው ተገልጿል።

በተመሳሳይ ከምባታ ጠምባሮ፣ ሀላባ፣ ሀዲያ ዞኖች እና  የየም ልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች ከጉራጌ እና ስልጤ ዞኖች ጋር በአንድ ላይ በመሆን አንድ የጋራ ክልል ለመመስረት የስልጤ ዞን ምክር ቤት እያካሄደ በሚገኘው 4ኛ ዙር 22ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ወስነዋል።  የክልል አደረጃጀት ጥያቄን ለመመለስ በመፍትሄነት በቀረበዉ መነሻ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ የውሳኔ ሀሳቡን ተቀብሎ ማፅደቁ ይታወሳል።

 የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር የስልጤ፣ የጉራጌ፣ የሀዲያ፣ የካምባታ ጠምባሮ ፣ የሀለባ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ ሕዝቦች ካለቸዉ መልካም ምድራዊና ሥነ ልቦናዊ የጋራ መስተጋብር አንፃር በአንድ አደረጃጀት እንዲሆኑ የሚል የዉሳኔ ሀሳብ መቅረቡን መናገራቸው ይታወሳል።

የደቡብ ክልል መንግስት ሰሞኑን የክልል አደረጃጀትን አስመልክቶ በዞን እና በልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች የተላለፉ ውሳኔዎችን “በሳል ውሳኔ” ሲል አድናቆት እና ምስጋና  አቅርቧል።ከዚህ በፊት በደቡብ ክልል ስር ተደራጅተው የነበሩት የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በህዝበ ውሳኔ የራሳቸውን ክልል መስረተው ከክልሉ መውጣታቸው የሚታወቅ ሲሆን በደቡብ ክልል ያሉት አስራ አንዱም ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች ባስተላለፉት ውሳኖዎች የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በሁለት ይከፈላል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.