ዜና፡ የምርጫ ቦርድ በደቡብ ኢትዮጵያ በተካሄደው ህዘበ ውሳኔ “አዲስ ክልል” ለማቋቋም የሚያስችል የመራጭ ድምጽ መስጠቱን አስታወቀ፤ በወላይታ የምርጫ አሰጣጡ ላይ ችግር እንደነበረ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14/ 2015 ዓ.ም፡– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ አምስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች በተካሄደው የሪፈረንደም ድምጽ አሰጣጥ አብዘሃኛው መራጭ አዲስ ክልል ለመመስረት የሚያስችል የድጋፍ ድምጽ መስጠቱን አስታወቀ።

ጥር 29 ቀን 2015 ድምጽ ከተሰጠባቸው አምስቱ ዞኖች እና አምስቱ ልዩ ወረዳዎች መካከል በወላይታ ዞን በርካታ ችግሮች የተስተዋሉበት በመሆኑ ውጤቱ ይፋ አለመደረጉን አመላክቷል። በወላይታ ዞን ቅድመ ምርጫ እና  በምርጫ ወቅት በርካታ ችግሮች መስተዋላቸውን እና ሪፖርት መደረጋቸውን ጠቁሟል።

የሂደቱን ሕጋዊነት ለማረጋገጥ አዳጋች ሁኔታ የፈጠሩ፤ በምርጫ ሕጉና አግባብነት ባላቸው መመሪያዎች መሠረት እንደ ከባድ የአሠራር ጥሠት የሚቆጠሩ ተግባራት ቁጥራቸው ጥቂት በማይባል የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ተፈጽመው በመገኘታቸው፤ የጥሰቶቹን ስፋት እና የሚሸፍኑዋቸውን ጣቢያዎች በተመለከተ ቦርዱ ተጨማሪ ምርመራ እንዲከወን አዟል ብሏል። የምርመራ ሥራው እንደተጠናቀቀም የመጨረሻውን ውሣኔ በጉዳዩ ላይ እንደሚሰጥም አሳውቋል።

ህዝበ ውሳኔ በተካሄደባቸው ዞኖች (በኮንሶ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጌዴኦ፣ በጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (በቡርጂ፣ በባስኬቶ፣ በአሌ፣ በአማሮ፣ በዲራሼ) የተደረገውን ቆጠራ መሰረት በማድረግ አብዘሃኛው መራጭ በጋራ አዲስ ክልል ለመመስረት መወሰኑን አስታውቋል።

በውጤቱ መሰረት የሚታይ የተቃውሞ ድምጽ የተሰጠበት ዞን የጌዲዮ ዞን መሆኑን የቦርዱ መረጃ አመላክቷል። በወላይታ ዞን የተከሰተውን ችግር ቦርዱ በዝርዝር አስቀምጧል። በመራጮች ምዝገባ ወቅት በመዝገቡ ላይ የሠፈረው የመራጮች ፊርማ በድምፅ መስጫ ቀን ከተፈረመው ፊርማቸው ጋር የተለያየ መሆን፣ በመራጮች መዝገብ ላይ ከሚጠበቀው በላይ ብዛት ያለው የጣት አሻራ ምልክት (በመራጮች ምዝገባ ወቅትና በድምፅ መስጫ ቀን) የተደረገ መሆኑ፣ የሚሉት ይገኙበታል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.