ዜና፡ ዐቃቤ ህግ ከባድ የሙስና እና አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ፈጽመዋል በተባሉ ሶስት የፖሊስ አባላት እና ግብረ-አበሮቻቸው ላይ ክስ መሰረተ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 9/2015 ዓ.ም፡- ዐቃቤ ህግ በአዲስ አበባ ፖሊስ የአየር መንገድ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ሀላፊን ጨምሮ ስልጣናቸውን አላግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና እና አስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈፅመዋል ባላቸው 3 የፖሊስ አባላት እና ግብረ-አበሮቻቸው ላይ ክስ መመስረቱን ፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ክሱ የተመሰረተው 1ኛ ተከሳሽ ም/ኢንስፔክተር መንግስቱ ገብረሚካኤል አልባሞ (በአ/አ/ ፖሊስ የአየር መንገድ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ሀላፊ)፣ 2ኛ. ዋና ሳጅን ቦሴ ለምለሙ ሙልዬ (ቦሌ ኤርፖርት ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ)፣ 3ኛ. ሻለቃ ዮሀንስ አበበ (በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ሰራዊት መኮንን)፣ 4ኛ. አደም ሰይድ መሀመድ (በግል ስራ የሚተዳደር) እና 5ኛ. ረዳት ሳጅን ተማም አቡራይ ልካሳ (በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል መከላከል አባል) ላይ ነው፡፡

የዐቃቤ ህግ ክስ እንደሚያሳየው የግል ተበዳይ የሙዚቃ መሳሪያዎች ከውጪ ለማስገባትና ጉዳይ ለማስፈጸም አርቲስት አረጋኸኝ ወራሽ ከተባለ ሙዚቀኛ በሚያዚያ 6/2014 ዓ.ም ውክልና ወስዳ አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 4, ሚሊዮን 534 ሺህ 203 ብር የሆኑ እቃዎችን ካስገባች በኃላ 4ኛ ተከሳሽ የአቶ አረጋኸኝ ወራሽ ውክልና ስላለኝ ንብረቱን አስረክቢኝ በማለት የግል ተበዳይን ሲጠይቃት እሷም እቃውን ለማስገባት ለጉምሩክ የከፈለችውን 1 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር እና ስራውን የሰራችበትን 2 ሚሊዮን ብር በድምሩ 3 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር በቅድሚያ እንዲከፍላት ትጠይቃለች፡፡

4ኛ ተከሳሽም ጉዳዩን በሕጋዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ከ1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር 3ኛ ተከሳሽ የመከላከያ ሰራዊት አባልነቱን በመጠቀም የወታደራዊ ደንብ ልብስ እንደለበሰ ካልተያዙት ግብራበሮቹ ጋር ወደ መኖሪያ ቤቷ በመሄድ በመዛት እና በማስፈራራት እንዲሁም በማሳሰር ብሎም ከታሰረችበት የፖሊስ ጣቢያ ሐምሌ 29/2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 10፡30 ሰዓት ሲሆን ወደ አየር መንገድ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ “ንብረቱን ካልመለስሽ ክሱን ወደ ሽብር ወንጀል እንቀይረዋለን እናሳይሻለን” በማለት እንዳስፈራራት ክሱ ያስረዳል፡፡

ቀጥሎም ከተበዳይ የግል ስልክ ላይ ንብረቱ ይገኝበታል ያሏቸውን ስልክ ቁጥሮች ከወሰዱ በኋላ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የአየር መንገድ ፖሊስ ጣቢያ የሴት እስረኛ ማቆያ እንደሌለው እያወቁ ሆን ብለው ለሌላ አገልግሎት ከሚጠቀሙበት መብራት እና መኝታ ከሌለው፣ በሩ ከውስጥ ከማይዘጋ እና ደህንነቱ ባልተጠበቀ ባዶ ክፍል ውስጥ እንድታድር የደረጉ ሲሆን በእለቱም 5ኛ የፖሊስ መለዮውን እንደለበሰና የጦር መሳሪያ እንደያዘ ወደ ክፍሉ በመግባት ‹‹ብትጮሂም ምንም አታመጪም፣ ማንም አይደርስልሽም፣ የግቢውን በር ቆልፌዋለሁ፣ ብቻዬን ነኝ፣ እጮሀለሁ ካልሽ በዚህ ክላሽ እመታሻለሁ›› በማለት የግል ተበዳይን በብርቱ ዛቻ በማስፈራራት መከላከል እንዳትችል በማድረግ አስገድዶ እንደደፈራት እና  ከአንድ ሰዓት በኋላ ተመልሶ በመምጣት ድጋሜ ተመሳሳይ ድርጊት እንፈፀመ ተገልጧል፡፡

የግል ተበዳይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ከተፈጸመባት በኃላም እዛው ክፍል ውስጥ ለ3 ቀን እንድታድር 1ኛ ተከሳሽ ትዕዛዝ በመስጠት፣ 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ ንብረቱን ብትመልስ እንደሚሻላት በመዛት ንብረቱን አስቀምጦ የነበረው ግለሰብ በወንጀል ባልተጠረጠረበትና ክስ ባልቀረበበት ሁኔታ በማታለል ወንጀል እንደተጠረጠረ አስመስለው በ1ኛ ተከሳሽ ትእዛዝ ሰጪነት የብርበራ ትእዛዝ አውጥተው በመኖሪያ ቤቱ ብርበራ ካደረጉ በኋላ ለጊዜው ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ላይ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 03-56045 ኦሮ የሆነ ዶልፊን መኪና እስከ ለሊቱ 6፡00 በማቆም ጫና በመፍጠር፣ ከፍተኛ ዛቻ እና ማስፈራሪያ በመፈጸም 4ኛ ተከሳሽ ንብረቱን የተቀበለ በመሆኑ፣ 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ እና 4 ኛ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል 5ኛ ተከሳሽ ደግሞ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

በተጨማሪም 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሽ ንብረቱ እሱ ጋር ይሆናል ብለው ያሰቡትን አቶ ቢኒያም ጳውሎስን ንብረቱን እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ሲዝቱና ሲያስፈራሩት ቆይተው በሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ሰዓቱ በውል ባልታወቀ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወንድማማቾች ስጋ ቤት አካባቢ 3ኛ ተከሳሽ ለጊዜው ካልታወቁ የመከላከያና የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ 5 ሰዎችና ሌሎች 2 ግለሰቦች ጋር በመሆን የግል ተበዳይ አቶ ቢኒያም ጳውሎስን ለመያዝ በመኪና በማባረር አራት ጥይቶችን በመተኮስ ከያዙት በኋላ 3ኛ ተከሳሽና ለጊዜው ያልተያዙት ተጠርጣሪዎች በመሳሪያ እየደበደቡ መኪና ውስጥ አስገብተው አይኑን በጨርቅ አስረው ወደ ጎልፍ ክለብ ወስደውታል፡፡

በዚህም ከሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በሕገ ወጥ መንገድ ጨለማ ክፍል ውስጥ ለ15 ቀናት አስረው ካቆዩት በኋላ ንብረቱን በሃይል ስላስመለሱ የግል ተበዳይን የለቀቁት በመሆኑ ሁለቱም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ህግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ጥቅምት 8 ቀን 2015 ቀን ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

ተከሳሾች የክሱ ማመልከቻ ደርሷቸው ከጠበቃ ጋር ለመቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.