ዜና፡ አሰመኮ በጋምቤላ ከተማ በሰብአዊ መብቶች ተቋም እና ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት መፈፀሙን ገለፀ፣ የፌዴራል እና የክልሉ የጸጥታ አካላት ጥቃቱን በአፋጣኝ እንዲያስቆሙ አሳሰበ

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የፎቶ ክሬዲት: africanchildforum.org

በአዲስ ስታንዳርድ ሪፖረተሮች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፤ መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በቡድን ሆነው የመጡ ሰዎች ወደ ኢሰመኮ ጋምቤላ ጽሕፈት ቤት በመሄድ የተለያዩ የጥፋት ድርጊቶችን መፈፀማቸውን እንዲሁም በኢሰመኮ ባልደረቦች ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ማድረሳቸውን እና በከተማዋ የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ሥራዎችን በሚያከናውኑ ሌሎች ድርጅቶች ላይ ተመሳሳይ ጥፋት አድርሰው ድርጅቶቹ “ከከተማው ለቅቀው እንዲወጡ” ማስፈራሪያ እና ዛቻ ማድረሳቸውን አስታወቀ። 

ኮሚሽኑ ይህ ማስፈራሪያ እና የጥፋት ድርጊቶች የተፈፀሙበት በጋምቤላ ከተማ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች፣ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) እና በጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) መካከል የተደረገው ውጊያን ተከትሎ በክልሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ታጣቂ ኃይሎች ቢያንስ 50 ሲቪል ሰዎች በተናጠል እና በጅምላ መገደላቸውን የሚያስረዳ ሪፖርት መስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ማውጣቱን ተከትሎ ነው፡፡

ኢሰመኮ ትላንት መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው በማኅበራዊ ትስስር ድረ ገጾች እና መገናኛ ብዙኃን የተሳሳተ፣ አነሳሽ እና ዛቻ ያዘሉ መረጃዎች ሲሰራጩ እንዲሁም በኢሰመኮ ባልደረቦች ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ መልእክቶች ሲዘዋወሩ ቆይተዋል፡፡

“…ይህንን ዐይነት በብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋም እና ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና በክልሉ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ምልከታ የሚጥል በመሆኑ የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት ተባብረው በአፋጣኝ እንዲያስቆሙ ኮሚሽኑ በጥብቅ ያሳስባል”

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ

በጋምቤላ ከተማ በብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋም እና ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረው ይህ ጥቃት በክልሉ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ምልከታ የሚጥል በመሆኑ የፌዴራል እና የክልሉ የጸጥታ አካላት በአፋጣኝ ሊያስቆሙ ይገባል ሲልም ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ በሕገ መንግሥት የተቋቋመ ፌዴራል የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋም መሆኑንና የኮሚሽኑ ሠራተኞችም በአዋጅ የልዩ መብት ጥበቃ የሚደረግላቸው መሆኑን አስታውሰው፣ “ኮሚሽኑ የክትትል እና የምርመራ ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት የተለያዩ ተግዳሮቶች የሚገጥሙት ቢሆንም፤ ይህንን ዐይነት በብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋም እና ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና በክልሉ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ምልከታ የሚጥል በመሆኑ የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት ተባብረው በአፋጣኝ እንዲያስቆሙ ኮሚሽኑ በጥብቅ ያሳስባል” ብለዋል።

ከሰኔ 7 እስከ ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጎጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች አሁንም ሟቾች የተቀበሩበትን ቦታ ለማወቅ እና ፍትሕ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ በመሆናቸው የኮሚሽኑ ምክረ ሃሳቦች በአፋጣኝ እንዲተገበሩ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በድጋሚ አስታውሰዋል።

በጋምቤላ ከተማ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች፣ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) እና በጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) መካከል የተደረገው ውጊያን ተከትሎ ከሰኔ 7 እስከ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በክልሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ታጣቂ ኃይሎች ቢያንስ 50 ሲቪል ሰዎች በተናጠል እና በጅምላ መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት  መስታወቁ ይታወሳል፡፡

የጋምቤላ መንግስት በጋምቤላ ክልል የመንግሥት ኮሚሽኑ ያወጣው ሪፖርት “ሚዛናዊነት ዮጎደለው የምርመራ ውጤት ” መሆኑን ጠቅሶ እንደማይቀበለው አስታውቋል። ኢሰመኮ መስከረም 18/2015 ዓ.ም ያወጣው ሪፖርት “በአጅጉን የተጋነነ ከመሆኑም ባሻገር መሬት ላይ ያለው ሃቅ ታሳቢ ያላደረገ ነው” ሲል የክልሉ መንግስት አክሎ ገልጿል።

ሪፖርቱ ከተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ማለትም መንግስት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂ ቡድንና ህውሓት ደጋፊዎች እንዲሁም በተለያዩ ወንጀሎች ሲጠረጠሩ ከነበሩ ግለሰቦች የተወሰደና በአንድ አካባቢ የታጠረ መሆኑን ነው የክልሉ መንግስት የገለጸው። አክሎም ሪፖርቱ የጋምቤላ ነባር ብሔረሰቦችን ከሌሎች አብረዋቸው ከኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ሆን ብሎ ለማጋጨት የተዘጋጀ መሆኑን በመግለጽ እንደማይቀበለው እና እንደሚያወግዘው  መግለፁ ይታወቃል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.