ዜና፡- አሜሪካ ኤርትራና ኢትዮጵያ “የጋራ ወታደራዊ ጥቃት” እንዲያቆሙ ጠየቀች፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ሃላፊ በሽሬ ሁለት የእርዳታ ሰራተኞች መቁሰላቸውን አረጋገጡ

አንቶኒ ብሊንከን

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 05/2015 ዓ/ም: የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል በሽሬ ዙሪያ በተከሰተው ግጭት እና እየጨመረ በመጣው ሁከት፣ የህይወት መጥፋትና ሰላማዊ ሰዎችንና ንጹሃንን ኢላማ ያደረገ ጥቃት አስመልክቶ እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች “አሜሪካን አሳስባታል” ብለዋል።

አሜሪካ “የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት በጋራ የሚያካሂዱትን ወታደራዊ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና ኤርትራም ጦሯን ከሰሜን ኢትዮጵያ ማዉጣት አለባት” ብላለች።  

አንቶንዮ ብሊንከን  “የትግራይ ባለስልጣናትም ከትንኮሳ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ” ጥሪ አቅርበዋል ።

ከአንቶኒ ብሊንከን ማግለጫ ጥቂት ቀደም ብሎ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታና አስቸኳይ ድጋፍ አስተባባሪ የሆኑት ማርቲን ግሪፍትስ ዛሬ በሽሬ በደረሰው ጥቃት ሁለት የእርዳታ ሰራተኞች መቁሰላቸውን አረጋግጠው “ከባድ ዉጥረት” መኖሩን ተናግሯል::

ማርቲን ግሪፍትስ የተጎዱትን እና የሰብአዊ ድርጅቶቻቸውን ስም አልጠቀሱም። 

ነገር ግን ጋዜጠኛ ሲሞን ማርክ እንደዘገበው በሽሬ በተደረገ የአየር ጥቃት ሁለት ንፁሀን ዜጎች ሲገደሉ በአለም አቀፉ ቀይ መስቀል የሚሰሩ ሁለት ሰራተኞች እና አራት ሲቪሎች በጥቃቱ ቆስለዋል።

ይህ አሜሪካ በተወሰኑ ቀናት ልዩነት ያወጣችዉ ሁለተኛው መግለጫ ነዉ:: ጥቅምት 2፣ ከአውስትራሊያ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ እና ዩናይትድ ኪንግደም ጋር በመሆን በሰሜን ኢትዮጵያ እየተባባሰ ያለውን ጦርነት ያወገዙ ሲሆን የኤርትራ ኃይሎች ወታደራዊ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያቆሙ አንዲሁም ከሰሜን ኢትዮጵያ እንዲወጡ ጠይቀዋል። በተጨማሪም ሁሉም የውጭ ተዋናዮች ይህንን ግጭት የሚያባብሱ ድርጊቶችን ማቆም አንዳለባቸው አሳስቦዋል።

አንቶኒ ብሊንክ ሙሉ መግለጫ

በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል በሽሬ ዙሪያ በተከሰተው ግጭት እየጨመረ የሚሄደው ብጥብጥ፣ የህይወት መጥፋት፣ በዘፈቀደ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ኢላማ ተደርጎ የደረሰው ጥቃት መሰረት አድርጎ የወጣው ሪፖርት አሜሪካ አጀጉን አሳስቧታል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ መከላከያ ሰራዊት እና የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት በጋራ የሚያካሂዱትን ወታደራዊ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና ኤርትራ ጦሯን ከሰሜን ኢትዮጵያ እንድታወጣ እንጠይቃለን። በተጨማሪም የትግራይ መከላከያ ሰራዊት ቀስቃሽ እርምጃዎችን እንዲያቆም እንጠይቃለን። በአማራ ክልል ቆቦ አካባቢ የትግራይ መከላከያ ሰራዊት ከነሐሴ 18 ቀን ጀምሮ በወሰደው እርምጃ ወደ ጦርነቱ እንዲመለስ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረከተ ሲሆን ይህም ለከፋ ጭፍጨፋ እና ለተጨማሪ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭነት አንዲኖረው አድርጎታል።

ሁሉም የታጠቁ ተዋናዮች ሰላማዊ ዜጎችን ማክበር እና መጠበቅ አለባቸው በተጨማሪም ለተቸገሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አካላት ያለ ምንም እንቅፋት ሰብአዊ አገልግሎት እንዲሰጡ እንጠይቃለን።

የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ሁሉንም ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና በአፍሪካ ህብረት መሪነት በሚካሄደው የሰላም ድርድር ላይ በስትክክል እንዲሳተፉ ደግመን እንገልፃለን። አሜሪካ  በተቻለ ፍጥነት የሰላም ንግግሮችን ለማደራጀት እና ለማስታረቅ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ መንግስታት እና ከሌሎች አለም አቀፍ እና አህጉራዊ አጋሮች ጋር ሙሉ በሙሉ ትሰራለች።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.