ዜና፡ በወልቂጤ ከተማ ኮማንድ ፖሰቱን እና የክላስተር አደረጃጀትን በመቃወም ሁለተኛ ዙር የስራ ማቆም አድማ እያደረጉ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገለፁ




ምስል ማህበራዊ ድህረገፅ

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20/2014 ዓ.ም፡- በወልቂጤ ከተማ ኮማንድ ፖሰቱን እና ክላስተርን በመቃወም የሁለት ቀን ስራ የማቆም አድማ እየተደረገ መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለፁ፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ የታዘዘው ኮማንድ ፖስት ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ባለመሆኑ የማህበረሰቡ የመንቀሳቀስ መብቱ መታገዱን ገልፀው ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ስራ የማቆም አድማ በማድረግ፣ ንግድ ተቋማትን በመዝጋትና፣ እንቅስቃሴውን በመገደብ ህገ መንግስታዊ መብቱን እየጠየቀ ነው ብለዋል.፡፡ አድማው ትናንት የጀመረ ሲሆን ጠቅሰው ዛሬም የሚደረግ መሆኑን አክለው ተናግረዋል፡፡

ምንም የፀጥታ ችግር ባልተከሰተበት ሁኔታ ኮማንድ ፖስት ታዞ የታጠቀ የፀጥታ ሃይል ማሰማራትና ህዙቡ እንዲሸበር ማድረግ የህግ አግባብነት የለውም ያሉት የከተማዋ ነዋሪው አቶ ተናኘ (ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው የተቀየረ)  ክላስተርን የተቃወሙ ወጣቶች ያለ ምንም ማዘዣ ወረቀት የህግ ከለላ በሌለበት  እ የ ታሰሩ በመሆኑ  ማህበረሰቡ ይህን በመቃወም አድማ አድርጓል ብለዋል፡፡

ሆቴሎች፣ የተለያዩ የንግድ ተቋማት፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዝግ መሆናቸውንም አክለው የገለፁት ምንጫችን መንግስት ለጥያቄአችን ትኩረት የማሰይጥ ከሆነ ይህ አድማ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በድጋሜ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡

ዛሬ የአድማው የመጨረሻ ቀን ነው ያሉት አቶ ተመስገን (ስማቸው የተቀየረ)  ሌላኛው ምንጫችን ትግሉን የሚመሩና በማህበረሰባችን ህልውና ላይ የፖሎቲካ ቁማር አንጫወትም ብለው ከሃላፊነት ተነስተው  ያለአግባብ የታሰሩ ሰዎች ስላሉ ጉዳያቸው ፍርድ ቤት ቀርቦ ውሳኔውንና  መንግስት የሚሰጠንን ምላሽ አይተን ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የምንታገል ይሆናል ብለዋል፡፡

ነሐሴ 18 ቀን የክልሉ ኮማንድ ፖስት ለሁለተኛ ጊዜ ባወጣው መግለጫ በከተማው የንግድ ሱቆችና የንግድ ድርጅቶች ያለምንም ምክንያት መዝጋትና በከተማው በቀን 19/12/2014 ዓ.ም ጀምሮ ባንኮች፣ የተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት መዝጋት እነደማይቻል አስታውቋል፡፡ አክሎም የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሬዎች ስራ ማቋረጥ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን ገልፆ ይህን ትእዛዝ በሚተላለፉ አካላት ላይ በዞኑ የተቋቋመው ጊዜያዊ ኮማንድ ፖሰቱ እርምጃ እንደሚወስድ ቢያሳስብም ህብረተሰቡ ግን የራሱን እርምጃ ከመተግበር ወደ ኋላ ሳይል ከትናንት ጀምሮ ዛሬ የሚያበቃ ስራ የማቆም አድማ አድርጓል፡፡

የደቡብ ክልል ኮማንድ ፖስት ነሐሴ 12/2014 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ላልተወሰነ ጊዜ በጉራጌ ዞን ወረዳዎችና ከተማዎች ማንኛቸውም መንግስታዊ ይሁን መንግስታዊ ያልሆኑ ስብሰባዎች እና ዉይይት ማድረግ መከልከሉ ይታወሳል

የክልሉ ኮማንድ ፖስት ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ማንኛውም ሰልፍና መሰል እንቅስቃሴዎችን ማካሄድ እና የንግድ ሱቆችና ተቋማትን ያለምንም ምክንያት መዝጋት የከለከለ ሲሆን የባጃጅ እንቅስቃሴ እስከ ምሽት 2 ሰአት ድረስ እንዲሁም የሞተር ሳይክል እንቅክቃሴ እስከ ምሽት 1ሰአት ብቻ እንዲሆን ገድቧል።

ኮማንድ ፖሰቱ በመንግሥት የስራ ሰአት የቢሮ ሀላፊም ይሁን ባለሙያ በቢሮ አለመገኘት እንደማይቻል ገልፆ ይህን ትእዛዝ በሚተላለፉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቁ የሚታወስ ነው።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.