ዜና፡ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በታንዛኒያ የተጀመረውን ውይይት ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እየሰተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2/ 2015 ዓ.ም፡- በምንግስትና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል በታንዛኒያ የተደረገው ውይይት ጥሩ መግባባት ላይ መድረሱን በመግለፅ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የተጀመረውን ውይይት ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እየሰተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሀይሉ አዱኛ ትላንት ለሚዲያ በሰጡት መግለጫ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ በውይይት ተፈቶ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው የሃሳብ ልዩነት በውይይት እንዲፈታ ለሰላም ትልቅ ትኩረት በመስጠት ከማንኛውም አካል ጋር ያለውን አለመግባባትን ለመፍታት እየሰራን ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

መንግስት በሰላም አስፈላጊነት ስለሚያምን የሃሳብ ልዩነት በውይይት እንዲፈታ ለሰላም ትኩረት በመስጠት ከማንኛውም አካል ጋር ግጭትን ለማስቆም ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል ሃላፊው፡፡

በታንዛኒያ በተደረገው ውይይት ጥሩ መግባባት ላይ መደረሱን የጠቀሱት ሀይሉ አዱኛ ውይይቱን ተጠናክሮ በማስቀጠል በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት መከፋፈልና መሰዳደብ አቁመው ለውይይቱ መሳካት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም አባ ገዳዎች እና እናቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በሁለቱ አካላት መካከል በታንዛኒያ ሲካሄድ በቆየው የሰላም ውይይት፣ ከስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉን ሚያዚያ 25 ቀን መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በተናጠል ባወጡት መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወቃል፡፡ ውይይቱ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ የተከናወነ ቢሆንም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ግን በዚህኛው የውይይት ምዕራፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ አልተቻለም ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ ገልጧል፡፡

የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትም በበኩሉ ባወጣው ምግለጫ በወሳኝ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ አለመደረሱን አስታውቋል፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከመግባባት ላይ መደረሱን ገልጧል፡፡

ሁለቱም ተደራዳሪ አካላት በቀጣይ ተገኛኝተው ውይይቱን በማስቀጠል በሰላማዊ መንገድ በዘላቂነት ግጭትን ለመፍታት መስማማታቸውን አስውቀው አሁንም ግጭትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.