ዜና፡ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በቆጂ ከተማ የታጠቁ ሀይሎች በከፈቱት ጥቃት ሁለት ፖሊሶችን ጨምሮ አራት ሰዎች ተገደሉ  

በቆጂ ከተማ፤ ፎቶ -ቪዚት ኦሮሚያ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14/2015 ዓ.ም፡- የአትሌቶች መፍለቂያ በመባል የምትታወቀው በቆጂ ከተማ የታጠቁ ሀይሎች አርብ ግንቦት 11 2015 በከፈቱት ጥቃት ሁለት ፖሊሶችን ጨምሮ አንድ የሚኒሻ አባልና አንድ የጥበቃ ሰራተኛ በድምሩ አራት ሰዎች መግደላቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለፁ፡፡

በከተማዋ ላይ ጥቃቱ የተፈፀመው የቱርዚም ሚንስቴሯ አምባሳደር ነሲሴ ጫሊ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሎ አብዲ፣ የአርሲ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ፋሮና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ሁለተኛው “ታላቁ የበቆጂ ሩጫ” ከተካሄደ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

ግንቦት 11፣ 2015 ከምስቱ 4 ሰዓት ጀምሮ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን የገለፀው አንድ ስሙ እንዲገለፅ ያለፈለገ የከተማዋ ነዋሪ ታጣቂዎቹ በከተመዋ የሚገኙ ሁለት ፖሊስ ጣቢያ ላይ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ተኩስ ምክፈታቸውን ገልፀው ከከተማው ፖሊስ ጣቢያ 8 እስረኞችን ማስለቀቃቸውን እንዲሁም በከተማዋ በሚገኘው የወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ላይ ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ ሁለት የፖሊስ አባላትን፣ አንድ የሚኒሻ አባልንና የጥበቃ ሰራተኛን ገድለዋል ብሏል፡፡ በባንኩ ላይ የመዝረፍ ሙከራ አለመደረጉንም አክሎ ገልጧል፡፡

ከ 4 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሰባት ሰዓት ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን የገለፀው  የከተማዋ ነዋሪ ታጣቂ ሀይሎቹ ጥቃቱን ተከፋፍለው መፈፀማቸውን ገልፀው መከላከያ ሰራዊት ከአሰላ ተነስቶ ወደ በቆጂ ከተማ ሲቃረብ ታጣቂ ሀይሎቹ ከተመዋን ለቀው መውጣታቸውን ተናግሯል፡፡

ታጣቂዎቹ በበቆጂ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት ከፍተው ካስለቀቁት ስምንት እስረኞች መካከል ስድስት የሚሆኑት በማግስቱ በፍቃዳቸው መመለሳቸውን ከፀጥታ አካል መስማታቸውን የከተማዋ ነዋሪ አክሎ ገልጧል፡፡

“በበቆጂ ከተማ ሁለት ፖሊስ ጣቢያ ነው ያለው አንደኛው የከተማው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የወረዳው ወይም የገጠር ፖሊስ ጣቢያ ነው፤ እኔ የምኖረው የወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ሰፈር ነው፤ ጣቢያው ላይ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ እየሰማሁ ነበር፡፡ በጥቃቱም ከፖሊስ እንድ ወንድ እና ሴት ፖሊሶች ተገድለዋል፡፡ በተጨማሪም አንድ የሚኒሻ አባልና የጥበቃ ሰራተኛ ህይወታቸው አልፏል” ሲል ስለ ሁኔታው ገልጧል፡፡

እንደ ነዋሪው ገለፃ  ከሆነ የከተማዋ የፀጥታ አካላት ታጣቂ ሀይሎቹ ይገባሉ ብለው ያሰቡበትን ማለትም በከተማስ በስተምስራቅ ጋለማ የሚባል ጫካ እና ካካ በሚባል ተራራ አካባቢን በመጠበቅ ላይ በመሆናቸው ብዙ ፖሊሶች በጣቢያዎቹ አነበሩም፡፡ ታጣቂዎቹ ይገባሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ሳይሆን ሌሙ በምትባል ከተማ በኩል እና በአጎራባው ቀበሌዎች በኩል በመግባታቸው ከተማ ለጥቃቱ ተጋልጣለች ሲል ገልጧል፡፡

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ የሆነው ሳምሶን (ለደህንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረ) በእለቱ እጅግ አስፈሪ የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ እንደነበር ገልፆ በጥቃቱ አራት ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከሟቾቹ አንዱ የሆነው የሚኒሻ አባል የተገደለው በመኖሪያ ቤቱ መሆኑን ገልጧል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ከተማዋ በተለመደው መደበኛ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደምትገኝ እና በከተማ ውስጥ ተጨማሪ የፀጥታ አካላት መግባታቸውን ነዋሪው አክለው ገልፆልናል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የከተማዋን ፖሊስ ጽ/ቤት እንዲሁም ከንቲባ ሁሲያ አብይን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ እያደረጉ ባሉት ስብሰባ ምክኒያት ሊሳካ አልቻለም፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.