ዜና፡ በአማራ ክልል በከባድ መሣሪያ ጭምር ታግዞ እየተካሄደ ባለው የተኩስ ልውውጥ በሲቪል ሰዎች ላይ የሞት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ደርሷል- ኢሰመኮ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 26/2015 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊትና ታጣቂዎች መካከል በከባድ መሣሪያ ጭምር ታግዞ እየተካሄደ ባለው የተኩስ ልውውጥ በሲቪል ሰዎች ላይ የሞት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ይህን የገለፀው በአማራ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” በሰብአዊ መብቶች ላይ ያለውን አንድምታና ተጽእኖ በተመለከተ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡

ኢሰመኮ መግለጫው በሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት ያለ መኖሩን ገልፆ በተለይ ሸዋ ሮቢት፣ አርማኒያ፣ አንጾኪያ፣ ገምዛ እና ማጀቴ በመከላከያ ሰራዊት እና በአካባቢው ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥና በከባድ መሣሪያ ጭምር የታገዘ ጥቃት እየተከናወነ መሆኑን ገልጧል፡፡

በዚህም ምክንያት በሲቪል ሰዎች ላይ የሞት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ደርሷል ያለው መግለጫው ከደሴ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በተለያዩ ጊዜያት የተዘጋ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል ብሏል።

በተጨማሪም በክልሉ ያሉ የተወሰኑ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማዋቀር ውሳኔን በመቃወም የተካሄዱ ሰልፎችን መርተዋል/አስተባብረዋል የተባሉ የተወሰኑ ወጣቶች እና ከፋኖ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ የተወሰኑ ሰዎች እንደታሰሩ አረጋግጫለው ሲል በመግለጫው አስታውቋል።

በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚፈጠሩ ተጨማሪ ግጭቶች ሰብአዊ መብቶች ላይ አስከፊ/ከባድ ጥሰቶች የሚያስከትሉ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች ችግሩን በሰላማዊ መንገድና በውይይት እንዲፈቱ፣ ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶችና ንግግሮች እንዲቆጠቡም ኢሰመኮ አስስቧል፡፡

በመጨረሻም ስለደረሰው ጉዳት ሁሉ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፣ በማናቸውም ሁኔታ የሚፈጸሙ እስራቶች ሕግን መሠረት ያደረጉ በተለይም “የጥብቅ አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነጻ መሆን” የሚሉትን የሰብአዊ መብቶች መርሆችን ያከበሩ መሆናቸውን መንግሥት እንዲያረጋግጥ ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.