ዜና፡ በሱማሌ ክልል የተከሰተው ድርቅ የበርካቶችን ህይወት ቀጥፏል፤ የወረዳው አመራር “ከአቅማቸው በላይ” መሆኑን ቢያምኑም የሟቾችን ብዛት ግን ውድቅ አድርጓል

 
ሞያሌ ወረዳ ኤል ጎፋ መጠለያ

በመድኃኔ እቁባሚካኤል @Medihane እና በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

ሞያሌ፣ መጋቢት 8/ 2015 ዓ.ም፡- በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ዞኖች አንዱ በሆነው በዳዋ ዞን፣ ከተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቅለው በሞያሌ ወረዳ በሚገኙ ሁለት የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች የተጠለሉ ከ18 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ተፈናቃዮች ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ። ተፈናቃዮቹ ያልተለመዱ ነገሮችን ለመመገብ እየተገደዱ ነው። የወረዳው ኃላፊዎች የችግሩን አሳሳቢነት በማመን “ከአቅማችን በላይ ሆኗል” ብለዋል።

አዲስ ስታንዳርድ በሞያሌ አቅራቢያ መለብ ቀበሌ በሚገኘው ሃርቦር ተፈናቃይ መጠለያ ባደረገው ጉብኝት በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ያገኛቸው አንድ ተፈናቃይ  አፋጣኝ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀው በማዕከሉ አካባቢ ከስምንት በላይ ሰዎች መሞታቸውን ተናግሯል። በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ሰዎች በሕይወት ለመትረፍ እየታገሉ መሆናቸውን እና የከብት መኖን(ፍሩሽካ) ለመመገብ መገደዳቸውን በመግለፅ የድርቁን አስከፊነት አስረድተዋል።

በለሄይ ከተማ  በስራ ላይ ሆኑ ያገኘነው የጤና ባለሙያ አደን አሊ በተለያዩ የሞያሌ ልዩ ቀበሌዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ቢያንስ ሶስት ህፃናት መሞታቸውን አረጋግጧል። የሟቾቹን ፎቶግራፎች ለአዲስ ስታንዳርድ ያሳየው አሊ፣ ከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳለ ገልፆ የህጻናትን ህይወት ለመታደግ የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት እንዲፋጠን ጠይቋል።

ቤተሰቦቹን ለመርዳት የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ከሞያሌ ከተማ ወደ ኤል ጎፋ መጠለያ ጣቢያ የገባው ወጣት አሊ እንደሚናገረው በስፍራው እርዳታ እየደረሰ ባለመሆኑ በድርቁ ቢያንስ አምስት ሰዎች ሞተዋል፡፡

ነገር ግን ከኡላጋ የመጡት እና አሁን በኤል ጎፋ የተፈናቃዮች ካምፕ ተጠልለው የሚገኙት አሊዮ ኢብራሂም እንደተናገሩት ድርቁ እስካሁን ከተፈናቃዮች ማእከል እስከ አስር የሚደርሱ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። አሊዮ በማዕከሉ ውስጥ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ተፈናቃዮች የምግብ፣ የህክምና ቁሳቁስ እና የመጠለያ እጥረት መኖሩን ለአዲስ ስታንዳርድ በእንባ ተሞልተው ገልፀዋል።

“እርዳታ እንዲያደርጉልን ብንጠይቅም መልስ አላገኘንም፣ የምንበላው ምንም የለንም፣ በረሃብ ውስጥ ሆነን እየጠየቅን ነው፣ አሁን እንኳ መቆም አልቻልኩም” ሲሉ በምሬት አሊዮ ገልፀዋል፡፡ “እዚህ ያለው ዋነኛ ችግር ምግብ፣ መድኃኒት እና መጠለያ ድጋፍ አለመኖር ነው። ዝናብ ከመጣ ሰዎች የሚጠለሉበት ቦታ አይኖራቸውም” በማለት፣ ውሃ ፍለጋ ወደ ኤል ጎፋ በመምጣት የቀሩትን ፍየሎች በመሸጥ ህይወታቸውን ለማቆየት እየጣሩ ያሉት አሊዮ ተናግረዋል።

አዲስ ስታንዳርድን ያነጋገራቸው ሌላ የመጠለያው ነዋሪ፣ በድርቁ ተፅዕኖ ምክንያት በተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ ከስምንት በላይ ሰዎች መሞታቸውን ገልፀዋል።

ከሙካቱ ወደ ኤል ወያ የመጡት አዛውንት ሳላዳ ሀሰን እንደተናገሩት ሁሉም ከብቶቻቸው ሞተዋል። “የምንበላው የለንም ምንም አላገኘንም፤ እስካሁን ሃንጃ ከሚባል ከዛፍ የሚገኝ ፈሳሽ ነበር ስንመገብ የነበረው፡፡ አሁን ግን ዛፎቹ ሙሉ በሙሉ ደርቀዋል” ሲሉ ሳላዳ ገልፀዋል፡፡

ቦኔያ አሊ የሚናገረው ተመሳሳይ ታሪክ አለው። ከጉጂ ወደ ኤል ጎፋ የተፈናቃዮች ካምፕ የመጣው ሙሉ ከብቶቹን በድርቁ ከሞቱበት በኋላ ነው። ልክ እንደሌሎች ሁሉ፣ እርዳታ እስኪመጣ በተስፋ የሚጠብቀው ቦኔያ ከሰል በማክስል የቤተሰቡን ህይወት ለመታደግ እየሞከረ ነው።

የእድሜ ባለፀጋው ማህሙድ ሞሃመድ ዝናብ የላስቲክ መጠለያቸውን እንዳያፈርስባቸው ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል፡፡ “ወደዚህ ከመምጣቴ ከስድስት ወር በፊት ሰማንያ ከብቶቼንና ሃያ አምስት ግመሎቼን አጥቻለሁ። አሁን እዚህ ህይወታችንን ለማስቀጠል ርዳታ እርዳታ እየጠበቅን ነው ”ሲሉ በሃርቦር መጠለያ ውስጥ የሚኖሩት ማህሙድ ተናግሯል።

የሞያሌ ወረዳ የአደጋ ስጋት አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳን መሀመድ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት በወረዳው በ14 የተለያዩ የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ 94,852 ተፈናቃዮች ሞኖራቸውን ጠቅሰው 8,808 የሚሆኑ አባወራዎች ወይም 52,852 የሚጠጉ ሰዎች በኤል ጎፋ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ መሆኑን ገልፀዋል።

ከክልሉ በተገኘው ውስን የእርዳታ ቁሳቁስ ከፍተኛ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 1 ሺህ 200 አባውራዎች ሩዝ፣ ዘይት፣ ስኳር እና ቴምር መከፋፈሉን ጠቁመዋል።

“ሰዎቹ እየገጠማቸው ያለው ዋነኛው ችግር የምግብ እና የመጠለያ እጥረት ነው። እዚህ የምትመለከቷቸው የፕላስቲክ መጠለያዎች [በፀሃይ እና ዝናባማ ቀናት] ለመኖር በጣም አስቸጋሪ ናቸው። የሚታየው የዝናብ ምልክት የሚቆይ ከሆነ መጠለያዎቹ እድሜ አይኖራቸውም” ሲል ኢሳን ተናግሯል።

“የምግብና የመጠለያ ጉዳይ ከአቅማችን በላይ ሆኗል” ሲል ኢሳን የገለፀው ሃላፊው “ጉዳዩን ወደ ክልሉ መንግስት አስተላልፈነዋል።” ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢሳን በተፈናቓዮቹ የቀረበውን የሟቾች ቁጥር ውድቅ በማድረግ በወረዳው ተለይተው በረሃብ መሞታቸው የተረጋገጠው አራት ብቻ ናቸው ብለዋል። አክለውም ቁጥሩን ከፍ ያደረጉት በሌሎች ጉዳዮች የሞቱትን ጭምር በማካተት ነው ብለዋል። ከሟቾቹ መካከል ሦስቱ ጎልማሶች ሲሆኑ የተቀረው የ16 ዓመት እድሜ ታዳጊ መሆኑን ሃላፊው አመላክቷል።

በአጠቃላይ በውረዳው 49,611 ግመሎች፣ 93,912 ከብቶች፣ 74,394 ፍየሎች እና 1,172 አህዮች በድርቁ መሞታቸውን ከኢሳን የገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የወረዳው የአደጋ ስጋት አመራር ባለሙያ አቶ መሀመድ ይስሀቅ ወረዳው “ባለው አቅም ለሁሉም ተፈናቃዮች ምግብ ማቅረብ እንደማይችል” በመግለፀ ይህ ከአቅማችን በላይ ነው  ብለዋል፡፡ አክለውም ጉዳዩን ለክልሉ አስተዳደር ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.