ዜና፡ በመንግስትና በቅዱስ ሲኖደስ መካከል የቃላት ጦርነት ተባብሶ ቀጥሏል፤ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ–ኃይል ሰልፍ እናዳይካሄድ ቢያስጠነቅቅም ሲኖዶሱ ሰላማዊ ሰልፉ ተፈጻሚ እንደሚሆን ገልጧል

አዲስ አበባ፣ የካቲት፣3/ 2015 ዓ.ም ፡- በመንግሥትና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መካከል የተፈጠረው  አለመግባባት እየተባባሰ በሄደበት ወቅት ሁለቱም ተቋማት ትላንት ከስዓት በኋላ የራሳቸውን አቋም የሚያንጸባርቅ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ መንግስት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተፈጠረውን አለመግባባት  እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው “መንግስትን በትጥቅ ሃይል ለመነቅነቅ” እየሰሩ ያሉ እና “ለዚህ አላማ  ወጣቶችን የሚመለምሉ” አካላት መኖራቸውን መረጃ ማግኘቱን አስታውቋል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣  የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ–ኃይል የተፈቀደ ሰልፍ የለም በማለት መግለጫ ቢሰጥም ፣ ሰላማዊ ሰልፉ በሀገራ አቀፍ ደረጃ በተያዘለት መርሃ-ግብር እንደሚከናወን ቅዱስ  ሲኖዶሱ አስታውቋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ አክሎም የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ–ኃይል የተሰጠው የሰልፍ ክልከላ መግለጫ መንግሥት አሁንም ችግሩን ለመፍታት ሳይሆን ቤተክርስቲያኒቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ለማውደምና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት የታወጀ አዋጅ መሆኑን “በጽኑ እንድናምን” አድርጎናል ብሏል፡፡

በማከልም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ውስጥ መሠረታዊ መብት ሆኖ የተጠቀሰ እና በሕገ መንግሥቱም አንቀፅ 30 ላይ በግልጽ የተደነገገ መሆኑን በመግለፅ መንግሥት ራሱ የሚመራበትን ሕገ መንግሥት ማክበርና ማስከበር ይኖርበታል ብሏል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ቤተ ክርስቲያን የእንቅስቃሴዋን አድማሱን በማስፋት በየካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ለማድረግ ያቀደችውንና ያሳወቀችውን ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ያለማንም ከልካይነት የምታከናውን መሆኑን ገልጧል፡፡ በራሷ አደባባይ በምታከናውነው ሰላማዊ ስልፍም የመንግሥት ድርሻ ሰልፉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የሲኖዶሱ መግለጫ፣ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ  ከመውጣቱ ጥቂት ቀደም ብሎ የወጣ ሲሆን፣ መግለጫው የተወገዙት ጳጳሳት ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት የተለዩ ቢሆንም ጽንፈኛ በሆኑ ፖለቲከኞች እንዲሁም የሌላ እምነት ተከታዮች ጭምር እየተደገፉ መሆኑን ገልጧል፡፡

“በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የቤተ  ክርስቲያን ክብርና ተቋማዊ ልዕልና ተጥሷል” ያለው ሲኖዶሱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖናዊ መርሆዎችና ይዞታ በመጣስ የተወገዘው ቡድን የቤተ ክርስቲያኒቱን ንብረት እንዲዘርፉ መንግስት ደግፏል ሲል በመግለጫው አብሯርቷል።

መንግሥት በበኩሉ “ባለሀብቶች፣ ፖለቲከኞች እና ከመንፈሳዊያን  ወጣቶች አደረጃጀቶች  የተውጣጣ ቡድን ከማዕከል  እስከ ታች ተደራጅቶ “የመስዋዕትነት ሰልፍ ‘ የተሰኘ ሰልፍ እያዘጋጀ መሆኑን ደርሼበታለሁ ብሏል። መግለጫው አክሎም ቡድኑ ወጣቶችን በመመልመል በተለያዩ መንገዶች እና በህገ ወጥ መንገድ ገንዘብ መሰብሰብ መጀመሩን ደርሼበታለሁ ያለ ሲሆን “ዕድሉን ተጠቅሞ መንግስትን በትጥቅ ሃይል ለማናወጥ” ፍላጎት አለው ብሏል፡፡ በተጨማሪም ቡድኑ ከተለያዩ የታጠቁ ሃይሎች ጋር ግንኙነት እየፈጠረ መሆኑን ደርሼበታሎ ሲል አክሎ ገልጧል።

“ለዚህ እኩይ አላማ አስቀድሞ አቅዶበት ያደረጀው  የሚዲያ ቡድን ስራውን መጀመሩ ተረጋግጧል” ሲል መንግስት በመግለጫ አመላክተዋል።

“በዚህም  የክትትል ሂደት ውስጥ የተለያዩ መሳሪያዎች የያዙ ሁከት ፈጣሪዎች በተሰማሩበት ወቅት ተይዘዋል፤  የቤተክርስቲያንን ደወል ላልተገባ ዓላማ በመጠቀም ለሁከትና ብጥብጥ የሚዳርጉ ቡድኖች ታይተዋል፡፡ በየአካባቢው ወጣቶችን ለግጭት  የሚመለምሉና  የሚያሰማሩ አካላት ተደርሶባቸዋል፡፡  በሃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማስፈጸም የሚሞክሩ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡የተሰጣቸውን ኃላፊነት ተጠቅመው የህዝብንና የእምነት ተቋማትን መብት በመጣስ የመንግስትን ስም ለማጥፋት የሚፈልጉ ስውር እጆችም እንዳሉም ታውቋል፡፡ ” ብሏል መንግስት በመግለጫው፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ እና በመንግሥት መካከል ያለው ውዝግብ የተባባሰው  በሦስቱ  ጳጳሳት እና  በ25 ሊቃነ ጳጳሳት ሹመት ጉዳይ በተፈጠረው ልዩነት የተነሳ ነው። ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጉዳዩ በውይይት እንዲፈታ ጥሪ አቅርበው የነበር ሲሆን፣ “የህዝብን መብትና ቋንቋን የመጠቀም ጥያቄን ሳይገታ መፍታት ይቻላል” ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተያየት በመቃወም መንግስት በቀውሱ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ አለው ሲል ከሷል።

የሁለት ቀን ጊዜ ገደብ እና ቀይ መስመር ማታለፍ

ቅዱስ ሲኖዶሱ ትላንት ባወጣው መግለጫ “የቤተክርስቲያን ቅጥሮች መሣሪያ በያዙ አካላትና በመንግሥት የጸጥታ መዋቅር በኃይልና በጉልበት ተወሯል፡፡ ሊቃነ ጳጳሳት አባቶች ለብዙ ዓመታት ከኖሩበት አህጉረ ስብከት ያለአንዳች የሕግ መሠረት በጸጥታ መዋቅሮች ተባረዋል፡፡ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብቶቻቸው ተገድቦም በግዞት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡ ወደ አህጉረ ስብከታቸውም ተመልሰው መግባት እንዳይችሉ እቀባ ተደርጎባቸዋል” ብሏል፡፡

በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ሻሸመኔ ከተማ  ቅዳሜ ጥር 27 በኦርቶዶክስ ምዕመናን እና በከተማ ፖሊስ መካካል በተነሳ ግጭት የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጧል፡፡ ግጭቱ የተቀሰቀሰው በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በአዲሱ “የኦሮሚያና ብሔሮች ብሔረሰቦች ቅዱስ ሲኖዶስ” የተሾሙ አባላት የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ በነበረበት ወቅት ነው።

በትላንቱ መግለጫ ቅዱስ ሲኖዶሱ በሻሸመኔ ሕገወጡን ቡድን በኃይል ለማስገባት በመንግሥት የጸጥታ መዋቅሮች በተወሰደ አሰቃቂ እርምጃ እስከ አሁን በደረሰን መረጃ ቁጥራቸው ከ30 በላይ የሚሆኑ ካህናትን እና አገልጋዮችን ጨምሮ የቤተ ክርስቲያናችን ልጆች ቅጥሯ አይደፈርም፣ ቤተክርስቲያን በተወገዙ ግለሰቦች አትረክስም በሚል ለሃይማኖታቸው ሰማእትነትን ተቀብለዋል ብሏል፡፡ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ልጆቿም በደረሰባቸው ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ምክንያት በሕክምና ላይ እንደሞገኙም አክሎ ገልጧል፡፡

ሰኞ ጥር 28 በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ልዩ ዞን ድንበር በተለምዶ ፊሊዶሮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቅድስት ለደታ ቤተ ክርስቲያን የተሰበሰቡ ሰዎች “የታሰሩ ሰዎች ይፈቱ” በማለት መንገድ በመዝጋት የፀጥታ ችግር ኢንዲከሰት በማድረግ በ19 ፖሊሶች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ማድረሳቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ መንግሥት በዚሁ አካሄድ ሕግ እየጣሰ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር እና ልእልና እያዋረደ የሚቀጥል ከሆነ ቤተ ክርስቲያን መንግሥት የጣሰውን ሕግ መሠረት በማድረግ ሰላማዊ የሆነውን እንቅስቃሴዋን አድማሱን በማስፋት መብቷን የምታስከብር መሆኑን አስታውቋል፡፡

መንግስት ከአጉል እልከኝነቱ ወጥቶ ከሕገ ወጦቹ ግለሰቦች ጋር በመተባበር በአደባባይ እየፈጸመ ያለውን የሕግ ጥሰት ዛሬን ጨምሮ በቀጣዮቹ ሁለትቀናት ውስጥ እንዲያቆም እና ሕግ እና ሥርዓትን እንዲያስከብር፣ በኃይል የወረራቸውን መንበረ ጵጵስና እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለቆ ለቤተክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መዋቅር እንዲያስረክብ ሲኖዶሱ በጥብቅ አሳስቧል፡፡ በተጨማሪም  ያለአግባብ ያሠራቸውን ካህናት እና ምእመናን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቅ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ለፈፀመው በደል በአደባባይ ይቅርታ እንዲጠይቅ፤ በካህናት እና ምእመናን ላይ ለደረሰው ሞት እና የአካል ጉዳት ተገቢውን ካሳ እንዲክስ እና የወደሙ ንብረቶቿን እንዲጠግን አክሎ ጠይቋል፡፡

መንግስት በበኩሉ “ጉዳዩ ቀይ መስመር አልፏል” ሲል ገልፆ  “የሰማዕትነት ሰልፍ” ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ የሚባል ነገር የለም ብሏል። በተጨማሪም “አገራዊ መረጋጋትን ለመፍጠር እና የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ሲባል የጸጥታ ሃይል ጠንካራ ህግ ማስከበር ስራ ውስጥ የሚገባ መሆኑን አስታውቋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.