ዜና፡ በሁለት ወራት ዉስጥ 28,000 ስደተኞች ከሳውዲ መመለሳቸው ተገለፀ

በብሩክ አለሙ

አዲስ አበባ፡ ግንቦት 19፣2014 ዓ.ም:- በሳውዲ አረቢያ እስር ቤት የነበሩ 28,000 ዜጎች በሁለት ወራት ውስጥ ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር አስታወቀ

ከሳዑዲ አረቢያ ወደ አገራቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያውያንን በበላይነት እንዲቆጣጠር የተቋቋመው ኮሚቴ ትናንት ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም ግምገማ አድርጓል። ባደረገው ግምገማም መንግስት ከስደት ተመላሾችን ለማስተናገድ   ፍራሽ፣ የግል ንፅህና መጠበቂያ  እና  ምግብ ነክ ነገሮች ያሟሉ ዘጠኝ ጊዜያዊ ማዕከላትን ማቋቋሙን ገልጿል።

ተመላሾቹን የመልሶ ማቋቋም፣ የመረጃ አያያዝ እና የስደተኞቹ ሻንጣዎች በጊዜ አለመድረስ  ጋር የተያያዙ ችግሮች መስተዋላቸውና እንዲሁም ሴቶችና ወንዶች ተመላሾችን በተመሳሳይ ጊዜያዊ ማቆያ  እንዲያስተናገዱ መደረጋቸው እንዱ ተግራሮት መሆኑ  ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ እና የኮሚቴው ሰብሳቢ  አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ኢትዮጵያውያንን ከሳዑዲ አረቢያ የመመለሱ ስራ በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት መቀጠሉን ገልፀው ከ7 እስከ 11 ወራት ውስጥ ወደ 100,000 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በመታቀዱ ባለድርሻ አካላት በትጋት በመስራት እቅዱን እንዲያሳኩ አሳስበዋል።

አምባሳደሯ ከታንዛኒያ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ የመን፣ እና ኦማን ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው የመመለስ እቅድ መያዙን ገልፀው መንግስት ዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ስራ ለመስራት  ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

አዲስ ስታንዳርድ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ለወራት በሳውዲ አረቢያ እስር ቤቶች  ኢ-ሰብአዊ በሆነ ችግር ውስጥ እንዳሉ ሲዘግብ መቆየቱ ይታወሳል። በርካታ ዘገባዎች የሳዑዲ ማረሚያ ቤቶች በስደተኞች ላይ ከሚወስዱት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በዋናነት  ኢትዮጵያውያን ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ አረጋግጠዋል። 

በሳውዲ አረቢያ ያሉ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መንግስት ከመጋቢት 21 ቀን ጀምሮ  ወደ አገራቸው የመመለስ ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስካሁን በተደረገ ጥረት 28,000 ስደተኞችን ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.