ዜና፡ ስልሳ ስምንት በመቶ በሊባኖስ የሚገኙ የሰው ቤት ሰራተኞች ለጾታዊ ትንኮሳ መዳረጋቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2/2015 ዓ.ም፡- በሊባኖስ በስደት ላይ ካሉት የቤት ሰራተኞች መካከል 68 ከመቶ ለጾታዊ ትንኮሳ መዳረጋቸውን አንደ አዲስ ጥናት አመለከተ::

እኛ ለኛ በስደት የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሊባኖስ ከሚገኘው የሊባኖስ አሜሪካን ዪኒቨርሲቲ ጋር  በመሆን ባዘጋጀዉ ጥናት መሰረት በርካታ ሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት እንደሚፈፀምባቸው አረጋግጠናል ብሏል።

ድርጅቱ ለአዲስ ስታንዳርድ በላከው መግለጫ ወደ 1000 የሚጠጉ የሰው ቤት ስራተኞችን አነጋግሮ መረጃ የሰበሰበ ሲሆን አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ገልፆ የጥናቱ ውጤት እንደሚያመለክተው በሊባኖስ በስደት ላይ ካሉት የሰው ቤት ሰራተኞች መካከል 68 ከመቶ ለጾታዊ ትንኮሳ ተደርገዋል ብሏል።

አስገድዶ መድፈርና ለመድፈር ሙከራዎች ማድርግን ጨምሮ የተለያዩ አይነት ጾታዊ ትንኮሳዎች አንደሚደርሱባቸዉ የገለጹት በጥናቱ የተሳተፉ ሴቶች ከፈቃድ ውጪ መሳም ማቀፍ እነ ሌሎች አካላዊ ንኪኪዎች ብአብዛኛዉ የሚደርስባቸው የትንኮሳ አይነት መሆኑን ተናግረዋል::

ትንኮሳዉ ከተፈጸመባቸዉ ሰቶች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ወይም ፈቃዳቸውን በአሰሪዎቻቸው የተነጠቁ ሲሆኑ 25 በመቶ የሚሆኑቱ ደግሞ ህጋዊ ፈቃድ ያላቸው መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል::
በተጨማሪም በጾታዊ ትንኮሳ የሚቀሰቀሰው ሃፍረት ምክንያት በርካታ ሴቶች የገጠማቸውን ላለማንሳት ወይ ለመርሳት እንደሚጥሩም ነው የተገለፀው። በዚህ ምክንያት ለጾታዊ ትንኮሳ የተዳረጉት ሴቶች ከ68 በመቶ በላይ ከፍ ሊል ይችላል የሚል ግምት አለን ሲል አክሏል ድርጅቱ።

የእኛ ለኛ በስደት መግለጫ እንደሚገልፀው የሊባኖስ መንግስት እአአ በ2020 ሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጾታዊ ትንኮሳ እንደ ወንጀል እንዲቆጠር “Law 205” የሚል ህግ ያጸደቀ ቢሆንም በስደት ላይ ያሉት በዚህ ህግ አለመካከታቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ከአፍሪካና እስያ የመጡ ስደተኛ ሴቶችን ለአደጋ መጋለጣቸው ያደረግነው ጥናት ያሳያል ብሏል።

በሊባኖስ ያሉት የሰው ቤት ስራተኞች ቁጥራቸው ከ300 ሺህ በላይ ሲሆን እንደ አምኔስቲ እንተርናሽናል መረጃ ከሆነ አብዛኛዎቹ (80%) ኢትዮጵያውያን ሴቶች ናቸው።

እኛ ለኛ በስደት የተሰኘው የግብረ ሰናይ ድርጅት እአኣ በ2017 በቤይሩት ሊባኖስ ተመስርቶ ላለፉት 6 አመታት በሊባኖስ የሚገኙት የሰው ቤት ስራተኛ ሴቶችን ሲያገለግል የቆየ ድርጅት ነው።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.