ዜና፡ ሴቶች በአዲስ አበባ ጎዳና ሰልፍ በመውጣት በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አቅረቡ

ሴቶች በአዲስ አበባ ከተማ የሰላም ጥሪ አያደረጉ ፡፡ ምስል- ማህበራዊ ድረ-ገፅ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 4/2014 ዓ.ም መቀመጫቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉ ሶስት ሴቶች ላይ ያተኮሩ ሀገር በቀል የሲቪክ ማህበራት ያዘጋጁት የሰላም ሰልፍ ትላንት ሀሙስ ጳጉሜ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡ የሰላም ሰልፉ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የእርስ በርስ ጦርነት እንዲያበቃ እና ሰላማዊ መፍትሄ እንዲሰጥ ጥሪ ያቀርቡበት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት (NEWA)፣ በአፍሪካ ቀንድ ሴቶች ስትራቴጅክ ኢኒሼቲቭ ኔትወርክ (SIHA) እና ትምራን የተደራጁ በርካታ ሴቶች የሰላም መልእክትን ያነገበ ባነር በመያዝ፣ የሴቶች የሰላም ሚና፣ እንዲሁም ከጦርነት ጋር ተያይዞ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የአስገድዶ መድፈር እና ጾታዊ ጥቃትን በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። በሰልፉ ላይ ይዘዋቸው የወጡት ባነሮች መካከል “በጦርነት የትኛውም አይነት አለመግባባት መፍትሄ አግኝቶ አያውቅም” ፣ “የሴቶች አካል የጦር ሜዳ አይደለም” ፣ “የሴቶች ሰውነት የጦር ሜዳ አይደለም” ፣ “ጦርነት የሞት፣ የረሃብ፣ የስደት እና የጥፋት መንስኤ እንጂ የልማት መሳሪያ አይደለም” የሚሉ ይገኙበታል፡፡

35 የሀገር በቀል የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ጳጉሜ 1ቀን 2014 ዓ.ም ባወጡት መግለጫ በኢትዮጵያ አፋጣኝ ሰላም እንዲሰፍን፣ በትግራይ እና ሌሎችም ግጭቶች በተከሰቱት አካባቢዎች የመሠረታዊ አገልግሎቶችና አቅርቦቶች እንዲጀመሩ፣. የፆታ ጥቃትን የፈፀሙ የተዋጊ አካላትን ጨምሮ ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ያደረሱ አካላት ላይ ምርመራ ተደርጎ የተጠያቂነት እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም ብሔር ተኮር ጥቃቶችና አግላይ ድርጊቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ከጠየቁ በኋላ በአገር በቀል ሲቪክ ማኅበራት የሰላም ጥሪ ሲያቀርቡ ይህ ሁለተኛው ነው።

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅት ምክር ቤት በፌዴራል መከላከያ ሠራዊትና በትግራይ ሃይሎች መካከል ወታደራዊ ጦርነት ካገረሸ በኋላ ጦርነቱ እንዲቆምና በአስቸኳይ ወደ ድርድር መድረክ እንዲመለሱ ጠይቀዋል።

ጦርነቱ በኢትዮጵያ ከድህነት እና ከትውልድ ቅራኔ በስተቀር የሚያመጣው አንዳችም ነገር እንደሌለ ማህበሩ የገለጸ ሲሆን ሲቪል ማኅበራት ድርጅቱ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተለይም ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ማለትም በህጻናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ አዛውንቶች እና የጥቃጡ ሰለባ በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ ሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ አስጠንቅቋል።

ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ዳግም የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ጦርነቱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመጉ)፣ አሜሪካ እና ቱርክን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና ተቋማት አውገዘዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪም ጦርነቱን ያወገዙ ሲሆን ሙሳ ፋኪ ከሁኔታው ጋር በተያያዘ ስጋት እንዳላቸው አንስተው የሰላም ድርድር እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ሰፊ የሰላም እና የድርድር ጥሪ ቢደረግም ጦርነቱ በገለልተኛነት የሚረጋገጡ ሪፖርቶች በሌሉበት ሁኔታ ቀጥሏል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.