ዜና፡ ማኅበረ ቅዱሳን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን “የማህበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያን” ያገደው  የመገናኛ ብዙኃኑን አዋጅ  በጣሰ መልኩ ነው ሲል ቅሬታ አቀረበ፤ እግዱን እንዲያነሳም ጥሪ አቅርቧል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14/ 2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያካሄደውን ስብሰባ የሚያውክና ህዝብን ለግጭት የሚያነሳሳ መልዕክት አሰራጭቷል፣ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን ተላልፏል በሚል እሁድ ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም የማህበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያን በጊዜያዊነት ማገዱን ተከትሎ፤ ጣቢያው ከመገናኛ ብዙኃን አዋጅ በሚቃረን ሁኔታ በባለስልጣኑ መታገዱን በመግለጽ ተቋሙን በበላይነት ለሚመራው ቦርድ ቅሬታ አቀረበ።

የማኅበረ ቅዱሳን በፃፈው ደብዳቤ “ቴሌቪዥን ጣቢያው ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ለማስተማርና ወቅታዊ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን ለማሳወቅ የተቋቋመ መንፈሳዊ ጣቢያ በመሆኑ የታገደበት የፕሮግራም ይዘት ከመገናኛ ብዙኃን አዋጁ ጋር የማይጋጭ መሆኑን እናምናለን” ሲል ገልጧል።

ጣቢያው አክሎም ለእግዱ ምክንያት የሆነውን መግለጫ በተመለከተ ማኅበሩ “ያስተላለፍነው መግለጫ በኢ/ኦ/ተ/ቤ ቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እውቅና ያላቸው ከ10 በላይ ማኅበራት ያሉበት ዐቢይ ኮሚቴ መግለጫ ነው ሲል ጠቅሶ መግለጫውን የማስተላለፍ ግዴታ አለብን ብሏል፡፡ ባለሥልጣኑ የወሰደው ርምጃ ግን በሃይማኖት የውስጥ ጉዳዮች ላይ ነው ብሏል፡፡

ባለሥልጣኑ ተጥሷል ያለው አንቀጽ 70 “ማንኛውንም ሃይማኖት ተኮር ፕሮግራም በሃይማኖት ተከታዮች መካከል እርስ በእርስ ግጭት ማነሳሳት፣ የሌሎችን ሃይማኖት ወይም እምነት ማንኳሰስ፣ ወይም በሃይማኖቶች መካከል አለመቻቻል እንዲፈጠር መቀስቀስ የለበትም” የሚል መሆኑን የጠቀሰው የማህበሩ ደብዳቤው፣ የተላለፈው ዘገባ ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር እንደማይገናኝ እና ማንኳሰስም እና መቻቻል እንዳይፈጠር የሚያደርግ አለመሆኑን አስረድቷል ።

ይዘቱ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት ይከበር በአባቶች መካከል የሚስተዋለው መከፋፈል ይቅር የሚል እንጂ ግጭት የሚፈጥር አለመሆኑን የገለፀው ደብዳቤው  ዘገባው በተሠራ ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ማን ምን አይነት ቅሬታ እንዳቀረበ ለጣቢያችን አልተገለጸም ብሏል።

የቀረበ ቅሬታ ካለም በአዋጁ መሠረት ባለሥልጣኑ ጣቢያችን ዘገባውን የሠራበትን ምክንያት መጠየቅና መረዳት አለበት ያለው ማህበረ ቅዱሳን ይህንን ባለማድረጉ ድርጊቱ በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ አንቀጽ 7 የተቀመጠውን የባለሥልጣኑን ገለልተኝነት እና ነጻነት የሚጋፋ ሆኖ አግኝተነዋል ሲል ገልጧል።

አክሎም ዘገባው ስሕተት ቢሆን እንኳ በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ እንቀጽ 73 የተቀመጠውን ከጽሑፍ ደብዳቤ እስከ የብሮድካስት አገልግሎት ባለፈቃድን ፈቃድ እስከማገድ ያሉ 4 ደረጃዎችን በመጣስ ያለማስጠንቀቂያና ውይይት፤ የአዋጁን አስተዳደራዊ ርምጃዎች ሂደት ያልተከተለ ውሳኔ ባለስልጣኑ በጣቢያው ላይ አስተላልፏል” ሲል ከሷል። በመጨረሻም ባለስልጣኑ እግዱን አንሥቶ ጣቢያው አገልግሎቱን እንዲቀጥል ማህበሩ በደብዳቤው ጠይቋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን እሁድ ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም የጣቢያውን ፍቃድ በጊዜያዊነት ያገደው ማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ በእለቱ  ሰበር ዜና በሚል ባሰራጨው መግለጫ ከሐይማኖት መገናኛ ብዙኃን ሚና ውጪ በሆነ አግባብ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያካሄደውን ስብሰባ የሚያውክና ህዝብን ለግጭት የሚያነሳሳ መልዕክት በማሰራጨቱ ነው ሲል መግለፁ ይታወቃል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.