ዜና፡የጋምቤላ ክልል መንግስት የኢሰመኮን ሪፖርት “ሚዛናዊነት ዮጎደለው የምርመራ ውጤት” በመሆኑ አልቀበለውም አለ

አቶ ኡገቱ አደንግ ፣ የጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ

በምህረት ገ/ክርስቶስ @Mercy

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23/2015 ዓ.ምየኢትዮጵያ ሰበአዊ መብት ኮሙሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም.በጋምቤላ ከተማ በተደረገ ውጊያ የጸጥታ ኃይሎች እና ታጣቂ ኃይሎች ቢያንስ 50 ሲቪል ሰዎችን በተናጠል እና በጅምላ ከህግ ውጭ መገደላቸውን የሚገልፀውን ሪፖርት “ሚዛናዊነት ዮጎደለው የምርመራ ውጤት ” ሲል የጋምቤላ መንግስት በጋምቤላ ክልል የመንግሥት ውድቅ አደረገ

ኢሰመኮ መስከረም 18/2015 ዓ.ም ያወጣው ሪፖርት “በአጅጉን የተጋነነ ከመሆኑም ባሻገር መሬት ላይ ያለው ሃቅ ታሳቢ ያላደረገ ነው” ሲል የክልሉ መንግስት ትላንት ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

ሪፖርቱ ከተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ማለትም መንግስት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂ ቡድንና ህውሓት ደጋፊዎች እንዲሁም በተለያዩ ወንጀሎች ሲጠረጠሩ ከነበሩ ግለሰቦች የተወሰደና በአንድ አካባቢ የታጠረ መሆኑን ነው የክልሉ መንግስት የገለጸው።

በተጨማሪም ሪፖርቱንም የጋምቤላ ነባር ብሔረሰቦችን ከሌሎች አብረዋቸው ከኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ሆን ብሎ ለማጋጨት የተዘጋጀ መሆኑን በመግለጽ እንደማይቀበለው እና እንደሚያወግዘው የክልሉ መንግስት ገልጧል፡፡

በጋምቤላ ከተማ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች፣ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) እና በጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) መካከል የተደረገው ውጊያን ተከትሎ ከሰኔ 7 እስከ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በክልሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ታጣቂ ኃይሎች ቢያንስ 50 ሲቪል ሰዎች በተናጠል እና በጅምላ መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መስከረም 18 ባወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

የክልሉ መንግስት በጋምቤላ ከተማ ኦነግ ሸኔ እና ጋነግ የፈጸሙትን ወረራ እና ጥቃት ብዥታ ተፈጥሮ የክልሉ መንግስት እና ሕዝብ የከፈለውን ተጋድሎ በዜሮ ያባዛ ነው ብሎታል፡፡ በተጨማሪም የመረጃ አሰባሰብባ ስነ ዘዴን የተቸው የክልሉ መንግስት፤ መረጃው ከተወሰነ ማለትም ከሕወሓት ደጋፊዎችና ኦነግ ሸኔ ደጋፊዎች የተወሰደ እንደሆነ ገልጧል፡፡

“ሪፖርቱ የክልሉን የፀጥታ ኃይል ሞራል የሚያዳክም፤ ፀረ-ሠላም ኃይሉንና መንግሥትን በአንድ ሚዛን ላይ አድርጎ ያየ፤ በአጠቃላይ ለጠላት የወገነ ሪፖርት ነው” ሲል የክልሉ መንግስት አክሎ ገልጿል።

ሰኔ 7 ቀን በጋምቤላ ከተማ ከጠዋቱ 12፡30 ጀምሮ በ”ጠላት ጦር” እና በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ እንደነበር የጋምቤላ ክልል መንግስት ዋቢ አድርጎ አዲስ ስታንዳር መዘገቧ ይታሳል። የጋምቤላ ክልል መንግስት ባወጣው መግለጫ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) እና መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነሰ) ጋር በመቀናጀት በጋምቤላና በአካባቢው ተኩስ መክፈታቸውን አስታወቋል፡፡

የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነሰ) ቃል አቀባይ በበኩላቸው የጋምቤላ ዋና ከተማን ለመቆጣጠር በቅንጅት ዘመቻ መጀመራቸውን ገልፀው ነበር፡፡በግምቢና ደምቢ ዶሎ ከተሞች የኦነግ ሃይሎች ከመንግስት ሃይሎች ጋር እየተዋጉ መሆኑንም አክሎ አስታወቋል፡፡

የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) በፌስቡከ ገፁ ዘመቻው የብልጽግና መንግሥት ሰራዊት ተቋማት፣ የብልጽግና መንግስት አመራሮች እና ሰራዊት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልፆ ማንኛውም ስቭል ማይበረሰብ የበራር ጥይቶች ሰለባ እንዳይሆን ከቤቱ እንዳይወጣ አሳስቧል፡፡ በተመሳሳይ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነሰ) አለምአቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳአ ታርቢ “የጋምቤላ ነፃነት ግንባር እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት የተቀናጀ ዘመቻ በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ ዋና ከተማ እየተካሄደ ነው” ብለው ነበር።

በወቅቱ የከተማው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ከተማዋ በጋምቤላ ነጻ አውጪ ግንባር እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ቁጥጥር ስር መዋሏን ገልጿል።

የክልሉ መንግስት “የመንግስት ሃይሎች ከፍተኛ ውጊያ ካደረጉ በኋላ የከተማዋን በከፊል ነፃ ማውጣት ተችሏል” ሲል ተጨማሪ መግለጫ ማውጣቱም ይታወሳል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.