ዜና፡ከትግራይና አዋሳኝ የአማራ ክልል አካባቢዎች ተፈናቅለው ከደቡብ ወሎ ዞን ጃሬ መጠለያ ጣቢያ ወደ አዋሽ ሰባት የተላለፉት ሰዎች የመንቀሳቀስ መብት በአፋጣኝ እንዲከበር ኢሰመኮ አሳሰበ

ምስል: የጃሬ የተፈናቃይ መጠለያን የሚያሳይ ፎቶ በቅርቡ በቻናል 4 ላይ ከቀረበ ዘገባ የተወሰደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9/2014 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ከጃሬ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ ወደ አዋሽ ሰባት የፌዴራል ፖሊስ ማሰልጠኛ እንዲዘዋወሩ የተደረጉ ከትግራይ ክልልና ክልሉን ከሚያዋስኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አፋጣኝ ምላሽ የሚያስፈልገው መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ

ኮሚሽኑ መስከረም 7 ባውጣው መግለጫ በጃሬ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የነበሩ ተፈናቃዮችን ሁኔታ ከግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ክትትል ሲያደርግ የቆየ መሆኑን ጠቅሶ፣ መጠለያ ጣቢያው በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች የሆኑ እና ከመሀል ትግራይ ከተሞች መቀሌ፣ አዲግራት፣ አክሱም፣ ሽሬ እና አካባቢው ተፈናቅለው የመጡ በወቅቱ 2,800 የሚሆኑ ሰዎች የሚገኙበት ነበር ብሏል ።

ሰዎቹ ከሌሎች የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች በተለየ መልኩ ከሕግ አግባብ ውጪ እና የመንቀሳቀስ መብታቸው ተነፍጎ፣ የሰብአዊ ድጋፍ በበቂ ሁኔታ ሳይቀርብላቸው በጃሬ መጠለያ ጣቢያ ለበርካታ ወራት ተይዘው ቆይተዋል ሲልም አክሏል፡፡

ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገበት ወቅት ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች ወደ ጃሬ መጠለያ ጣቢያ እንዲገቡ ሲደረግ “የጸጥታ ሥጋት ሁኔታ እስከሚጣራ ድረስ ነው የምትቆዩት” በሚል የተነገራቸው መሆኑን የገለጹ ቢሆንም፤ ማጣራት ሳይደረግ ለረዥም ወራት በቂ የሰብአዊ ድጋፍ በሌለበት እና ከእስራት ጋር በሚመሳሰል ነገር ግን ከቤተሰብ ለመገናኘት በማይቻልበት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲቆዩ መደረጋቸውን ተመልክቻለው ብሏል።

ለተፈናቃዮች የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብአዊ ድጋፎችን ለማቅረብ ጥረት ሲያደርግ የቆየው የፌዴራል አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ባለሙያዎች በአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች እና ታጣቂዎች በደረሰባቸው ተጽዕኖ ሥራቸውን ለማቋረጥ መገደዳቸውን ለመረዳት ተችሏል ያለው የኮሚሽኑ መግለጫ በክትትል በወቅቱ መጠለያ ጣቢያው በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ሥር የነበረ በመሆኑ አጋር የሰብአዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ድጋፍ ለማድረግ ተነሳሽነት ባለማሳየታቸው ተፈናቃዮች ለከፍተኛ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እጥረት መዳረጋቸውን፣ እንዲሁም በመጠለያ ጣቢያው የሕክምና አገልግሎት ያልነበረ በመሆኑ ተፈናቃዮች የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጭምር በመጠለያ ጣቢያው የጸጥታ አካላት የበላይ ኃላፊዎች በሚሰጥ ፍቃድ ብቻ እና በክፍያ በሚደረግ እጀባ ለመንቀሳቀስ ተገደው የነበረ መሆኑን አስረድቷል።

ኢሰመኮ በጃሬ የመጠለያ ጣቢያ የነበረውን አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በክትትል ከለየ በኋላ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መንግሥት ተቋማት የሁኔታውን አሳሳቢነት በመግለጽ ተፈናቃዮቹ በሕግ አግባብ በቁጥጥር ስር የዋሉ ባለመሆናቸው የመንቀሳቀስ መብታቸው ሊረጋገጥላቸው የሚገባ መሆኑን ሲጠይቅ መቆየቱን ገልፆ አስፈላጊ የሆኑ ሰብአዊ ድጋፎች እና የሕክምና አገልግሎቶች ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮችን ፍላጎቶች ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲቀርቡ የሚያሳስቡ የቃልና የጽሑፍ መልእክቶችና ምክረ ሃሳቦች በማስተላለፍ ተፈጻሚነቱን ለማረጋገጥ ከተቋማቱ የበላይ ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲደርግ ቆይቷል ብሏል።

ነገር ግን በተፈናቃዮች ሁኔታ ላይ ተጨባጭ መሻሻል ሳይታይ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በቅርቡ በድጋሚ መቀስቀሱን ተከትሎ በጃሬ መጠለያ ጣቢያ የነበሩ ተፈናቃዮች አዋሽ ሰባት ወደሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም እንዲዘዋወሩ ተደርገዋል ሲል ገልጿል ። ኮሚሽኑ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ተፈናቃዮችን በመጎብኘት አሁን የሚገኙበትን ሁኔታ ክትትል ለማድረግ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት ጠቅሶ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች የኮሚሽኑን ጉብኝት በአስቸኳይ እንደሚያመቻቹ አሳስቧል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንደገለጹት ለሕዝብ ጸጥታ፣ ደኅንነት እና ጤና ወይም የተፈናቃዮችን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሲባል በተፈናቃዮች እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ሊጣል የሚችልበት ሁኔታ ቢኖርም፤ የዚህ አይነቱ ገደብ የአስፈላጊነት፣ ምክንያታዊነት እና ተመጣጣኝነት መርሆችን በጥብቅ በተከተለ መንገድ ሊከናወን የሚገባው መሆኑን አሳስበው “በአዋሽ ሰባት የፌዴራል ፖሊስ ማሰልጠኛ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች የመጡባቸውን የትግራይ ክልል አካባቢዎች ብቻ መሰረት በማድረግ ለተራዘመ ጊዜ የመንቀሳቀስ ነጻነታቸውን ተነፍገው እንዲቆዩ መደረጉ የአስፈላጊነት፣ ምክንያታዊነት እና የተመጣጣኝነት መርሆዎችን የሚቃረን ነው” ብለዋል።

ዶ/ር ዳንኤል አክለውም ተፈናቃዮቹ በሕግ አግባብ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ባለመሆናቸው በመካከላቸው የጸጥታ ሥጋት ናቸው በሚል በምክንያታዊነት የሚጠረጠሩ ሰዎች ካሉ በመለየት፣ በመመርመር እና በሕግ አግባብ ተጠያቂ የማድረግ ሥራው ግልጽ እና ሕጋዊ በሆነ መንገድ በአፋጣኝ እንዲከናወን አሳስበዋል። አክለውም ሌሎች ተፈናቃዮች ሁሉ የመንቀሳቀስ መብታቸው በአስቸኳይ ሊረጋገጥላቸው፤ በመጠለያ ጣቢያዎች መቆየት የሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮችም የሲቪል ባሕርይ ወዳለው ጣቢያ ሊዘዋወሩ፤ እንዲሁም በቂ ምግብ፣ መጠለያ፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ፣ አስፈላጊ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ ሕክምና ወዘተ ሊቀርቡላቸው በሚችል ሁኔታ ውስጥ ሊሆን እንደሚገባ አሳስቧል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.