ዜና፡ በአማራ ክልል 520,000 ተማሪዎች ፍትሃዊ የሆነ መሰረታዊ የትምህርት እድል ተደራሽነት አለማግኘታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅታ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27/2015 ዓ.ም፡­- በአማራ ክልል 520,000 ተማሪዎች (ከዚህ ውስጥ 250,000 ያህሉ የተፈናቀሉ ህጻናት ናቸው) ፍትሃዊ የሆነ መሰረታዊ የትምህርት እድል ተደራሽነት አለማግኘታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰበዓዊ መብቶች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስታወቀ።

ድርጅቱ ሀሙስ ጥር 25/ 2015 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት እንዳስታወቀው ከእነዚህ አጠቃላይ ከ520ሺ ተማሪዎች ውስጥ በሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ እና ዋግ ኽምራ ዞኖች የሚገኙ 255,000 የሚያህሉ ህጻናት የትምህርት ቁሳቁስና የትምህርት ቤት ምገባ ያስፈልጋቸዋል ብሏል። መምህራን እና ሌሎች የትምህርት ቤት ሰራተኞች የመማር ማስተማር ሂደትን ለማስቀጠል የአዕምሮ እና የስነ-ልቦና ድጋፍ እርዳታ ይፈልጋሉ ሲለ አክሎ አስውቋል።

ከኦሮሚያ የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች አሁንም ወደ አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎ እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች እየገቡ መሆናቸውን ገልጧል። በተጨማሪም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ 41ሺ የሚሆኑ ስደተኞች በደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች ያረፉ ሲሆን እርዳታ እንደሚሹም ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

ጥር 14 ቀን ከኦሮሚያ የተፈናቀሉ 1,500 ዜጎች በሰሜን ወሎ ዞን ጃራ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የተጠለሉ ሲሆን፣ 1,800 የሚሆኑት ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን ወደሚገኘው የቱርክ መጠለያ ላይ ሰፍረዋል፡፡ በአጋር ወይም በአቅም ውስንነት ምክንያት በጤና፣ በምግብ እርዳታ በቂ አለመሆኑም ተመላክቷል።

በዋግ ኽምራ ዞን፣ ደብረ ብርሃን፣ ቀበሮ ሜዳና ጎልማሳ የሚገኙት ጃራ፣ቱርክ፣ ሲቴ እና ወለህና ቲሪኪ መጠለያ ጣቢያ ለተጠለሉ 45ሺ ተፈናቃዮች የውሃ ማመላለሻ ለሽከርካሪ ድጋፍ መደረጉንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰበዓዊ መብቶች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አክሎ ገልጧል።  በተጨማሪም በወሎ፣ ዋግ ኽም እና በሌሎች ደቡብ ጎንደር ወረዳዎች ለመገኙ ወደ 663ሺ የሚጠጉ ሰዎች በ5 ዙር የምግብ እርዳታ ያገኙ ሲሆን ይህም እስከ ጥር 18 ቀን በአማራ ክልል የምግብ እርዳታ የተደረገላቸው ሰዎች ቁጥር 2.5 ሚሊዮን አድርሶታል ብሏል።

ይህ በእንዲህ እያለ የአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች እንዲሁም ግጭት በነበረባቸው የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ከ6 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ወገኖች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች መኖራቸውን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢያሱ መስፍን ጥር 26 ቀን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለፁ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ800 ሺህ በላይ ያህሉ የጸጥታ ችግር ካለባቸው የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ መሆናቸውን ጠቅሰው 75 ሺህ ወገኖች በ40 ጊዜያዊ መጠለያዎች እንደሚገኙ እና ቀሪዎቹ ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ተጠግተው እንደሚኖሩ አስረድተዋል።

ከምግብ አቅርቦት አኳያም እንደ ክልል ከ6 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ወገኖች ድጋፍ እንደሚሹ መረጃን መሰረት በማድረግ ተለይቶ ለፌደራል መንግሥት መላኩን ጠቅሰው፥ ከዚህ ውስጥ የፌደራል መንግሥት ለ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ያህሉ መፍቀዱን ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት በኩል የሚቀርበው ድጋፍ ጊዜውን ካለመጠበቁ በተጨማሪ መቅረብ የሚገባውን ድጋፍ ዓይነቶች (ፓጃኬጁን) ያሟላ አለመሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡ በእነዚህ እና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች ተፈናቃዮች እና የምግብ እጥረት ያለባቸው ወገኖች ለከፋ ችግር ተዳርገዋል ብለዋል ኃላፊው፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.