ዜና፡- ህፃናትን ጨምሮ 48 ኤርትራውያንን በህገወጥ መንገድ ወደ ኬንያ ሲያዘዋውር የነበረ የፖሊስ አባል በቁጥጥር ስር መዋሉ ተዘገበ

ህፃናትን ከህገወጥ ዝውውር እንታደጋቸው

አዲስ አበባ፣ጥቅምት16/ 2015 ዓ.ም፡- የኤርትራ ዜግነት ያላቸው 23 ወንዶች ፣ 20 ሴቶች እና አምስት ህጻናትን በህገወጥ መንገድ ወደ ኬንያ ሊያሻገር የነበረ የደቡብ ኦሞ ዞን ፖሊስ አባል በህግ ቁጥጥር ስር መዋሉን የደቡብ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የሚዲያ ክፍል ሀላፊ ምክትል ኮማንደር ታጁ ነጋሽ ለብስራት ራዲዮ እንደተናገሩት ፤ በዞኑ ፖሊስ የትራፊክ ክፍል ዉስጥ የቴክኒክ ሀላፊ የነበረ ምክትል ኢ/ር አይተነዉ መኮንን፤ ተጓዦቹን በአይሱዙ የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪ በመጫን ወደ ኬንያ ድንበር ለማሸጋገር ሲሞክር ሀመር ወረዳ ላይ ጥቅምት 8 ከምሽቱ 4 ሰዓት ገደማ በዞኑ ፖሊሶች እና በክልሉ ልዩ ሀይል መያዛቸዉን ገልጸዋል።

ምክትል ኮማንደር ታጁ ፤ የደቡብ ኦሞ ዞን ኢትዮጵያን ከኬንያ እና ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያዋስን ድንበር እንደመሆኑ በአካባቢዉ ህገወጥ የሰዎች ዝዉዉር እና ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች እንደሚከናወኑ ጠቅሰው የክልሉ ልዩ ሀይል እና የዞኑ ፖሊስ በድንበሩ አካባቢ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ላይ ናቸዉ ብለዋል።

በቀጣይ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኤርትራውያን ተጓዦቹን ለፌደራል ፖሊስ እንደሚያስረክብ እንዲሁም ሲያጓጉዙ የነበሩ የፖሊስ አባል እና ሁለት ግለሰቦች ላይ ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን የደቡብ ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ክፍል ሀላፊ ምክትል ኮማንደር ታጁ ነጋሽ አክለው ተናግረዋል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.